ዓለምአቀፋዊ ዜና

የሜታ ቢዝነሥ ባለቤት ማርክ ዙከርበርግ በከብት እርባታ ሥራ ተሠማሩ

By Alemayehu Geremew

January 10, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሜታ ቢዝነሥ ኩባንያ ባለቤት እና ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ማርክ ዙከርበርግ ካላቸው ሥራ በተጨማሪ በከብት ዕርባታ የሥራ መስክ መሠማራታቸውን አስታወቁ፡፡

የከብት ዕርባታ ሥራውን የጀመሩት ከባለቤታቸው ጋር በመሆን በአሜሪካ ሃዋይ ግዛት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

“በዚህ ሥራዬ ማሳካት የምፈልገው በዓለም ከፍተኛ ጥራት ያለው ሥጋ ማቅረብ ነው” ብለዋል፡፡

በከብት ዕርባታ ሥራቸውም “ዋግዩ” እና “ኤንገስ” የተሠኙ እጅግ ውድ የሥጋ ወይፈኖችን እንደሚያደልቡ አመላክተዋል፡፡

በተጨማሪም የወተት ላሞችንም ጭምር  እንደሚያረቡ ነው የጠቆሙት፡፡

የሚደልቡት ከብቶችም በከብት ዕርባታው እርሻ የሚለማውን “ማካዴሚያ” የተሠኘ የቅባት እህል ተክል እንደሚመገቡ ጠቅሰዋል፡፡

ልጆቻቸውም ለከብቶቹ መኖ የሚሆነውን ተክል በመትከል እና በመንከባከብ እንደሚያግዟቸው ነው የገለጹት፡፡

ማርክ ዙከርበርግ በፈረንጆቹ 2004 ላይ ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የክፍል ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ፌስቡክ የተሰኘውን የማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡