ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ ከአፍሪካ አገራት ጋር ዲፕሎማሲዋን ማጠናከር አለባት-ምሁራንና ፖለቲከኞች
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ በአፍሪካ አገራት ላይ የዲፕሎማሲ ስራዋን አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት ምሁራንና ፖለቲከኞች ተናገሩ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና÷ኢትዮጵያ ግብፅ የምታደርገውን ዓለም አቀፍ ጫና ለመመከት በአፍሪካ ሀገራት ላይ የዲፕሎማሲ ስራዋን አጠናክራ መቀጠል አለባት ብለዋል።
“የህዳሴው ግድብ ጉዳይ በቀዳሚነት የሚመለከተው ሶስቱን ሃገራት (ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን) ሲያልፍም አፍሪካዊያንን ነው” ያሉት ፕሮፌሰሩ ኢትዮጵያ የምትከተለው ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በብዙ የአፍሪካ ሃገራት የሚደገፍ ነው ብለዋል።
የሶስቱን ሃገራት ጉዳይ ከአፍሪካውያን ውጭ አሳልፎ መስጠት ከፍትሃዊነቱ ይልቅ ጉዳዩ ለፖለቲካ አጀንዳነት እንዲውል ያደርገዋል ነው ያሉት።
ከሶስቱ ሃገራት ባለፈ ለቀጠናውና ለአህጉሪቱ ሰላም እንደማይጠቅም ጠቁመው÷ ኢትዮጵያ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው አፍሪካዊያን ጋር የዲፕሎማሲ ትስስሯን ልታጠናክር ይገባታል ብለዋል።
ከዚያም ባለፈ የሃገር ውስጥ ፖለቲካውን በማስተካከል በብሄራዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ ያለውን አንድነት ማጠናከር ያስፍልጋል ነው ያሉት ።
በሃገር ውስጥ ባሉ ፖለቲከኞች መካከል ምንም አይነት የሃሳብ ልዩነት መንሸራሸሩ የዴሞክራሲ መገለጫ ቢሆንም ህዝብን፣ ሃገርንና ሉአላዊነትን አደጋ ላይ በሚጥል ጉዳይ ላይ ግን ልዩነት መኖር የለበትም ብለዋል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ በበኩላቸው÷በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት ያላካተተ የቅኝ ገዥዎች ስምምነት በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የለውም።
በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንዲህ አይነት ተግባራትን ለማስቀጠል መሞከርም ከሰብአዊነት ያለፈና ኢትዮጵያ የማትቀበለው መሆኑን አብራርተዋል።
አያይዘውም ግድቡ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን እንደመሆኑ በተጠቃሚነት ጉዳይ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በጥብቅ የሚመለከተው ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።