Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የደረሱበት ሥምምነት የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በር ይከፍታል – ቲቦር ናዥ

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የደረሱበት ሥምምነት ዘመን ተሻጋሪ ግንኙነት በመመሥረት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በር የሚከፍት መሆኑን በኢትዮጵያ የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደር ቲቦር ናዥ ተናገሩ።

አምባሳደር ቲቦር ናዥ ከሶማሊላንድ ክሮኒክል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ÷ ኢትዮጵያ የወደብ አሥፈላጊነትን በተመለከተ ከወራት በፊት ይፋ ያደረገችው ሐሳብ  ጎረቤት ሀገራትን ተጠቃሚ ከማድረግ ያለፈ ምንም ጉዳት እንደሌለው አስረድተዋል።

የሀገራቱ ሥምምነት ÷ መሠረተ ልማቶችን በጋራ ለማስፋፋት፣ የኢኮኖሚ ትሥሥርን ለማሳደግ ፣ ሠላምና መረጋጋትን እውን ለማድረግ ብሎም የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የደረሱበት ሥምምነት በርካታ ደረጃዎችን ያለፈና በደንብ የታሰበበት እንደሆነ በመጥቀስ በቀጣይም አብረው ሊሰሩባቸው የሚችሉ በርካታ ስምምነቶች ሊፈጸሙ እንደሚችሉም ጠቅሰዋል።

ሥምምነቱ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን በእጅጉ ሊደግፍላት የሚችል የባሕር በር የሚያስገኝ ሲሆን ለሶማሊ ላንድም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥና ለበርካታ ዜጎቿ ሠፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር በኩል ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የደረሱበት ሥምምነት ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በጋራ እንዲሠሩ በር የሚከፍት መሆኑንም ተናግረዋል።

ቲቦር ናዥ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ እና በጊኒ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር በመሆን መሥራታቸውንም ኢዜአ ጠቁሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.