ኮሚሽኑ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው 30 ሚሊዮን ዜጎች ሃብት እያሰባሰበ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብሔራዊ አደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው 30 ሚሊየን ዜጎች ሃብት እያሰባሰበ መሆኑን አስታወቀ።
የሚሰበሰበው ሀብት በኮሮና ቫይረስና በሌሎች ምክንያቶች ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ለመደገፍ የሚውል ነው ተብሏል።
ኮቪድ-19 ከተከሰተ በኋላ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያሉ አረጋውያን፣የጎዳና ተዳዳሪዎችና በዕለት ገቢ የሚተዳደሩ 15 ሚሊየን ዜጎች ድጋፍ ፈላጊ መሆናቸው ተገልጿል።
ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ÷ኮሚሽኑ በቫይረሱ ምክንያት በሚከሰት የኢኮኖሚ መቀዛቀዝና በሌሎች ምክንያቶች ለችግር ለተጋለጡ ዜጎች ድጋፍ የሚያስፈልገውን 1ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር እያሰባሰበ ነው ብለዋል።
ለዚህም ኮሚሽኑ ከገንዘብ ሚኒስቴርና ከተባባሪ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን አመልክተው÷ባለሃብቱም ተሳትፎውን የሚያጎለብትበት መንገድ መፈጠሩንም አቶ ምትኩ ተናግረዋል።
መንግሥትም በጀት በመመደብ ዜጎች ድጋፍ እንዲያገኙ በመስራት ላይ እንደሚገኝ አስረድተው÷እስከ መስከረም 2013 ዓ.ም ድረስ ድጋፉን በማሰባሰብ ለተረጂዎች በዓይነትና በገንዘብ እንደሚከፋፈል ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።
በተለይም ሀብቱ የበረሃ አንበጣና የጎርፍ አደጋዎች ለሚያስከትሉት ችግር በአስቸኳይ ምላሽ በመስጠት ዜጎችን ለመደገፍና ለማቋቋም እንደታሰበም ነው የገለጹት።
ከዚያም ባለፈ በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረውን የምግብ ባንክ ለማጠናከር ይውላልም ነው ያሉት ።
በተያያዘም በገጠር የአገሪቱ አካባቢ ያሉ ዜጎች ኮቪድ-19 እና ግብርናን በማጣጣም ምርታማነት ሳይቋረጥ አርሶ አደሩ በሽታውን የሚከላከልበትን መንገድ ለመፍጠር ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።
አርሶ አደሩ ርቀቱን ጠብቆ ሥራውን እንዲያከናውን ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን አቅም እንደሚያሳድግ አቶ ምትኩ አመልክተዋል።
በዋናነትም አርሶ አደሩን ወደ ዘመናዊ አስተራረስ ዘዴ በማስገባት ከንክኪና ከስጋት ነጻ ሆኖ ምርትና ምርታማነትን ያሳድጋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።