በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ17 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ዋጋ ያለው ሥራ ተከናወነ
አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ሥድስት ወራት በሀገር አቀፍ ደረጃ በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች 17 ቢሊየን 598 ሚሊየን 796 ሺህ 561 ብር ዋጋ ያለው ሥራ መከናወኑን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በተካሄደው የክረምት እና የበጋ ወቅት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በ13 የስምሪት መስኮች 23 ሚሊየን 541 ሺህ 601 ወጣቶች መሳተፋቸው ተገልጿል፡፡
በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱም 54 ሚሊየን 676 ሺህ 327 የማሕበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ሥራዎች መከናወናቸውን የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ቡድን መሪ አቶ መላኩ ባዩ ተናግረዋል፡፡
ወጣቶች በመንግሥትና በማሕበረሰቡ ያልተሸፈኑ የልማት ሥራዎችንና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን መድረሳቸውንም ነው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የገለጹት፡፡
ከተከናወኑት ሥራዎች መካከልም÷ የአረንጓዴ ዐሻራ፣ የትራፊክ ደኅንነት፣ የአካባቢ ጽዳት፣ የደም ልገሳ፣ የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳትና የሰብዕና ግንባታ ማዕከላት፣ የሰላም ዕሴት ግንባታ፣ ሕገ-ወጥ የሠዎች ዝውውርና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መከላከል፣ የማጠናከሪያ ትምህርትና ሰብዕና ልማት ላይ ያተኮሩ ሥልጠናዎች እንደሚገኙበት አብራርተዋል፡፡
“በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ 2” በሚል መሪ ሐሳብ ከተካሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተጨማሪ ወጣቶች በወሰን ተሻጋሪ መርሐ-ግብር ተሰማርተው ለማሕበረሰቡ ካበረከቱት አገልግሎት ባሻገር÷ በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በወጣቶች ዘንድ ሀገራዊ አንድነት ለመፍጠር እና የባሕል ትስስሩንም ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራትን መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት በክረምቱና በበጋው መርሐ-ግብር እንደሀገር የተካሄደው የበጎ ፈቃድ ሥራ ስኬታማ ነው ብለዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው