የቱሪስት መስህቦችን ለ2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ለማስጎብኘት ዝግጅት ማድረጉን የአፋር ክልል ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል የሚገኙ የቱሪስት መስህቦችን በውጭ ለሚኖሩ 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ለማስጎብኘት ዝግጅት ማድረጉን የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል፡፡
የቢሮው ሃላፊ አቶ አሕመድ አብዱልቃድር ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በአፋር ክልል ያለው የቱሪዝም እንቅስቃሴ እየተነቃቃ መጥቷል።
በውጭ የሚኖሩ 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን እንዲጎበኙ የቀረበው ጥሪም የክልሉን ቱሪዝም ይበልጥ እንደሚያነቃቃው ተናግረዋል።
ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ለኢትዮጵያውያኑ በክልሉ የሚገኙ መስህቦችን ለማስጎብኘት አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
በዚህ መሰረትም በ2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሊጎበኙ የሚችሉ የቱሪስት መዳረሻዎች መለየታቸውን ጠቅሰው፤ ዳሎል፣ ኤርታሌ፣ አፍዴራ ሐይቅ እና የሉሲ ድንቅነሽ መገኛ ሃዳር ከተለዩ መዳረሻዎች ውስጥ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በእነዚህ አካባቢዎች የእንግዶችን ቆይታ ስኬታማ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
በተለይም ሆቴሎች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ኢትዮጵያውያኑን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ለጎብኚዎች የአፋርን ሕዝብ ባህል፣ እሴት፣ የአለባበስ ሥርዓት፣ ባህላዊ ምግቦች፣ ባሕላዊ ጭፈራዎች እና ሌሎች ክዋኔዎችን ለማሳወቅም በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
ስለሆነም በውጭ የሚኖሩ 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው በመምጣት የአፋርን ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ መስህቦችን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ