የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ለመደገፍ የጥናትና ምርምር ተቋማት የበኩላቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ለመደገፍ የጥናትና ምርምር ተቋማት የበኩላቸውን እንዲወጡ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጥላሁን ከበደ ጠየቁ፡፡
በአዲሱ የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ እና በተኪ ምርት ስትራቴጂ ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር የተዘጋጀ የምክክር መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እና የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበልን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡
በኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና በክልሉ ጥምረት በተዘጋጀው መድረክ ላይ በአምራች ኢንዱስትሪ ውጤታማነት እና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ምክክር እንደሚደረግ ተመላክቷል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ጥላሁን ከበደ በዚሁ ወቅት÷ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማሳደግ በአዲሱ የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ ላይ በልዩ ትኩረት መስራት ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም ተናግረዋል።
የውስጥ አቅምን በማጠናከር የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማሳደግ በክልሉ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
ዘርፉን ለመደገፍ የጥናትና ምርምር ተቋማት ሚናቸው የላቀ በመሆኑ የበኩላቸውን እንዲወጡም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል፡፡