Fana: At a Speed of Life!

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከ34 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ2015/2016 የምርት ዘመን ከለማው መሬት ከ34 ሚሊየን በላይ ኩንታል ምርት መገኘቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ፡፡

በክልሉ ግብርና ቢሮ የኤክስቴንሽን እና ግብዓት ዘርፍ ምክትል ሃላፊ አቶ አጥናፉ ባቡር እንዳሉት÷በክልሉ በምርት ዘመኑ ለማልማት ከታቀደው 1 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር መሬት አብዛኛውን በሰብል መሸፈን ተችሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት የመኸር ሰብል አሰባሰቡ ሒደት ከ80 በመቶ በላይ መጠናቀቁን የገለጹት አቶ አጥናፉ÷ በዚህም ከ34 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን አንስተዋል፡፡

ማሽላ፣ በቆሎ፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ አኩሪ አተር፣ ሰሊጥ፣ ኑግ እና ለውዝ ከተመረተው ሰብል መካከል እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡

በምርት አሰባሰብ ሂደት የሚያጋጥመውን ብክነት ለማስቀረት በተለይም በኩታ ገጠም እና ሰፋፊ እርሻዎች የምርት መሰብሰቢያ ኮምባይነር ለማቅረብ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ያልተሰበሰበው ቀሪው ምርት እስከ ጥር ወር መጨረሻ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ መናገራቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

አርሶ አደሩ በተለይ በበጋው ወቅት ሊከሰት በሚችል ሰደድ እሳት ሰብሉ እንዳይጎዳበት በፍጥነት መሰብሰብ እንዳለበት ተመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.