Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ በፌዴራል መንግሥት ባለቤትነት የተያዙ የልማት ድርጅቶች አዋጅን አጸደቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ባካሄደው 11ኛ መደበኛ ስብሰባ በፌዴራል መንግሥት ባለቤትነት የተያዙ የልማት ድርጅቶች አዋጅን አስመልክቶ የቀረበለትን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ አጽድቋል።

የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ መሐመድ አብዱ (ፕ/ር)÷የመንግሥት ልማት ድርጅቶች የኮርፖሬት ፋይናንስ ሥርዓታቸውን በማዘመን ተወዳዳሪነታቸውንና ውጤታማነታቸውን በማጠናከር የንግድ አሰራራቸውን ለማስፋፋት ነባሩን አዋጅ በአዲስ መተካት ማስፈለጉን አስረድተዋል፡፡

መንግሥት ሕዝብን ወክሎ ተግባሩን ሲያከናውን ተጠያቂነትን በሚያሰፍን መልኩ በግልጸኝነት ተግባርና ሃላፊነቱን መወጣት እንዲችል የአዋጁ መውጣት ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የምክር ቤት አባላቱ በበኩላቸው÷ አዋጁ የሕዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንዲቻል አዋጁን በጥራት ለማውጣት ቋሚ ኮሚቴው ያደረገውን ጥረት ማድነቃቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታውር እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)÷ በፌዴራል መንግሥት ባለቤትነት የተያዙ የልማት ድርጅቶች አሠራራቸውን አዘምነው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አዋጁ ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የምክር ቤት አባላትም በቀረበው ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ ቢጨመሩ ወይም ቢቀነሱ ያሏቸውን ሐሳቦች አንስተው ሰፋ ያለ ክርክር ከተደረገበት በኋላ ረቂቅ አዋጁ፣ አዋጅ ቁጥር 1314/2016 ሆኖ በሙሉ ድምፅ ጸድቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.