ስንወረር ድምጻቸው ያልተሰማ ዘላቂ ጥቅማችንን ለማረጋገጥ እውነታን መሰረት አድርገን ስንነሳ ጩኸትና ጫናው ብዙ ነው – አቶ ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ስንወረር ድምጻቸውን ያላሰሙ ዘላቂ ጥቅማችንን ለማረጋገጥ እውነታን መሰረት አድርገን በምናደርገው አንድ እርምጃ ሁሉ ጩኸትና ጫናው ብዙ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡
አቶ ደመቀ በኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ሳምንት ዓውደ ርዕይ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም÷ በየዘመኑ ያጋጠሙንን ፈተናዎች ተቋቁመን ብሄራዊ ጥቅማችንን እያስከበርን የመጣነው በህብረታችን እና በጠንካራ አንድነታችን ነው ብለዋል፡፡
ለአብነትም በቅርብ ጊዜ የነበሩ ፈርጀ ብዙ ጫናዎችን ተቋቁመን የዘለቅነው በሕዝባችን ጽናት እና አብሮነት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ጽኑ ሕዝብ ብርቱ ሀገር ያሉት አቶ ደመቀ÷ አሁን የሚታዩትን ጫናዎች ተቋቁመን ብሄራዊ ጥቅማችን በዘላቂት የምናስከብረውም ውስጣዊ አንድነታችን በማጠናከር እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ከታሪክ እንደተማርነው፤ አሁንም እንደሚታየው የሀገራችንን መጠንከር በበጎ የማይመለከቱ ሃይሎች አሉ ነው ያሉት፡፡
ስንወረር ድምጻቸውን ያላሰሙ ዘላቂ ጥቅማችንን ለማረጋገጥ እውነታን መሰረት አድርገን በምናደርገው አንድ እርምጃ ሁሉ ጩኸትና ጫናው ብዙ ነው ሲሉም አንስተዋል፡፡
ይህም በመጪው ዘመን ምን ያህን ፈተና እና ምንያህል የተጠናከር ሥራ እንደሚጠይቀን የሚሳይ ነው፤ ከዚህ ተጽዕኖ ለመውጣትም የድላችን አልፋ እና ኦሜጋ ውስጣዊ ጥንካሬጣችን ነው ብለዋል፡፡
ጠንካራ ዲፕሎማሲ እና የውጭ ግንኙነት መሰረቱ የውስጥ ጥንካሬ እና አብሮነት ስለሆነ በሁሉም መስክ ኢትዮጵያ አሸንፋ እንድትዘልቅ ማንውኛውንም የውስጥ ችግር ከሃይል አማራጭ በራቀ አግባብ በመደማመጥ በሰላም መፍታት ይገባል ብለዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ