Fana: At a Speed of Life!

የዳታ ልማት ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ቁልፍ አስቻይ በመሆኑ በትብብር ሊሰራበት ይገባል – በለጠ ሞላ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዳታ ልማት ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ቁልፍ አስቻይ በመሆኑ በትብብር እና በርብርብ ልንሰራበት የሚገባ ታላቅ ሀብት ነው ሲሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ሚኒስቴሩ ከተባበሩት መንግስታት የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ጉዳዮች ክፍል ጋር የዳታ ልማት እና አስተዳደር ረቂቅ መመሪያ ላይ የባለድርሻ አካላት፣ አመራሮች እና ተወካዮች በተገኙበት ውይይት አካሒዷል።

በለጠ ሞላ (ዶ/ር ) በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ከዳታ ልማት ውጭ የሚታሰብ አይደለም፡፡

ስለሆነም የዳታ ልማት ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ቁልፍ አስቻይ በመሆኑ በትብብር እና በርብርብ ልንሰራበት የሚገባ ታላቅ ሀብት ብለዋል፡፡

የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታውን የማስተባበር ሃላፊነት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ቢወስድም ለስኬታማነቱ ግን ሁሉም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በቅንጅት እንዲሰሩ አስገንዝበዋል።

ከትብብር መስኮቹ አንዱ የዳታ ልማት መሆኑን ያወሱት ሚኒስትሩ÷ የዳታ ልማትን በተገቢው ደረጃና ሒደት ለመምራት መሰል መመሪያዎች እንደሚያስፈልጉ ገልፀዋል።

የመመሪያው ዓላማም በተቀናጀ አግባብ እና በትብብር መንፈስ ውድ የሆነውን የዳታ ሃብት ለማልማት የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ሁሉ የሚተባበሩበትንና በቅንጅት ውጤታማ ተግባራትን ለማከናወን የሚሰሩበትን መድረክ ለመፍጠር እንደሆነ አመላክተዋል።

መመሪያውን ወደ ቀጣይ የማፀደቅ ሒደት በመውሰድ በአጭር ጊዜ ወደ ትግበራ ለማስገባት እንደሚሰራ ገልፀዋል።

በተባበሩት መንግስታት፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ክፍል ተወካይ ዋይ ሚን ክዎክ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ መንግሥት የዳታ ልማት እና አስተዳደር ላይ እየሰራቸው ያሉ ተግባራትን አድንቀው በቀጣይም በትብብር የሚሰሩ ሥራዎችን አጠናክረን እናስቀጥላለን ብለዋል።

በመድረኩ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ እቅድ እና ልማት ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት፣ የስፔስ ሳይንስ እና የጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ የመረጃ መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ የብሔራዊ መታወቂያ እና የኢሚግሬሽን እና የዜግነት ጉዳዮች አገልግሎቶች ተቋማት ተሳትፈዋል፡፡

የመመሪያውን አስፈላጊነት እና ጠቀሜታ ያወሱት ተሳታፊዎች መመሪያው በፍጥነት ወደ ትግበራ እንዲገባ ጥሪ ማቅረባቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.