አሜሪካና ብሪታኒያ የሁቲ አማፂያን ይዞታዎችን መደብደባቸው ተነገረ
አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ እና ብሪታኒያ በየመን የሁቲ አማፂያን ይዞታዎች ናቸው ያሏቸውን አካባቢዎች መደብደባቸው ተነገረ፡፡
ሀገራቱ በዛሬው ዕለት በጥምረት እርምጃ የወሰዱት አማፂያኑ ለሣምንታት በቀይ ባሕር ቀጣና ጥቃት ሲፈፅሙ መቆየታቸውን ተከትሎ እንደሆነ ዘ ታይምስ ኦቭ እስራዔል ዘግቧል፡፡
በጥቃቱ ዓየር ማረፊያ፣ ዓየር መንገዶች እና የጦር ካምፕ መመታታቸውን የሁቲ አማፂዎቹ የቴሌቪዥን ጣቢያ አል-ማሲራህ ዘግቧል፡፡
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን በበኩላቸው÷ እርምጃ የተወሰደው የሁቲ አማፂያን በሚጠቀሟቸው ሰው አልባ ድሮኖች፣ ባላስቲክ እና ክሩዝ ሚሳኤሎች እንዲሁም የድንበር እና የዓየር ክልል መቆጣጠሪያ ራዳሮች ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢራን፣ ሄዝቦላህ እና የሃማስ ቡድኖች ሀገራቱ በጥምረት ያደረሱትን ጥቃት ማውገዛቸው ተመላክቷል፡፡
ድብደባው “የየመንን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነትን የጣሰ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሕጎችን፣ ደንቦችን እና መብቶችን የገረሰሰ ነው” ሲሉም ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን÷ አጸፋዊ እርምጃ የወሰድነው አማፂያኑ በቀይ ባሕር ቀጣና ተደጋጋሚ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ ነው ብለዋል፡፡
እንደ አሥፈላጊነቱ ሀገራቱ በጥምረት ተጨማሪ ወታደራዊ እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ እንደማይሉም አመላክተዋል።