ሀሰተኛ ሰነዶችና የተቋማት ማህተም ሲያዘጋጅ በቁጥጥር ስር የዋለው ግለሰብ በ10 ዓመት እስራትና በገንዘብ ተቀጣ
አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶችንና የተቋማትን ማህተም ሲያዘጋጅ በቁጥጥር ስር ውሏል ተብሎ ክስ የቀረበበት ግለሰብ በ10 ዓመት ጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጣ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ወሰነ።
የቅጣት ውሳኔ የተወሰነበት ግሩም ክፈተው ገ/ህይወት በጥቅምት 22 ቀን 2015 ዓ.ም “በአዲስ አበባ የካ ክ/ከተማ ወረዳ 12 በቤት ቁጥር አዲስ በሆነ ህንጻ ላይ በተከራየው ክፍል ውስጥ የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶችንና የተቋማት ማህተሞችን እየቀረፀ ሲያዘጋጅ እንደነበር ተጠቅሶ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 (1) ሀ እና የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 (1) ሀ ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፏል” በማለት ሀሰተኛ ሰነዶችን ማዘጋጀት ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦበታል።
ይህ ክስ ከቀረበበት በኋላ ተከሳሹ የሰጠውን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች አቅርቧል።
ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ በተከሰሰበት ድንጋጌ እንዲከላከል ብይን የሰጠ ቢሆንም ተከሳሹ በተገቢው የዐቃቤ ሕግ መከራከሪያ ማስረጃን ያላስተባበለ በመሆኑ እንዲከላከል በተባለበት ድንጋጌ የጥፋተኝነት ፍርድ ተሰጥቶበታል።
ዐቃቤ ሕግ ላቀረበው የቅጣት ማክበጃ አስተያየት ፍርድ ቤቱ በመካከለኛ ደረጃ እንዲያዝ አድርጓል።
ተከሳሹ ለህዳሴ ግድብ የፈጸመውን የቦንድ ግዢ፣ የደም ልገሳ ያደረገውን ተሳትፎ ጠቅሶ ባቀረበው የቅጣት ማቅለያ አስተያየትን በሚመለከት ደግሞ ፍርድ ቤቱ የተለዩ በበጎ ፍቃድ የሰጠው የማህበራዊ ተሳትፎን በወንጀል ህግ አንቀጽ 86 መሰረት እንደ አንድ ማቅለያ በመያዝ እንዲሁም የቀደመ የወንጀል ሪከርድ እንደሌለውና የዘወትር ፀባዩ መልካም እንደነበር በወንጀል ህግ አንቀጽ 82 (1) ሀ መሰረት እንደ አንድ ማቅለያ ይዞለታል።
በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ ተከሳሹን በመካከለኛ ደረጃ በ10 አመት ጽኑ እስራትና በ6 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።
ታሪክ አዱኛ