Fana: At a Speed of Life!

የአቪዬሽን የሰው ሀይል ልማት ላይ በጋራ መስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአቪዬሽን የሰው ሀይል ልማት ላይ በጋራ መስራት የሚያስችል ስምምነት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ፣ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አየር ሀይል እና የኢትዮጵያ ኤሮ ክለብ ተፈራርመዋል።

በመድረኩ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈርሃት ካሚል እንዳሉት÷ ልጆቻችን ተገቢው እውቀት እና ብቃት ኖሯቸው የአቪዬሽን ዘርፉ ላይ እንዲሰሩ የተደረገው ስምምነት ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቴ÷ መጭውን የዓለም የአቪየሽን ስርዓትን በተገቢው መንገድ ለመምራት የሰው ሀይል ልማቱ ጠንካራ መሰረት የያዘ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው÷ ለቀጣይ የዓለም የአቪዬሽን እና ኤሮስፔስ ዘርፍ ኢትዮጵያ በጥራትና በብዛት የሰለጠነ የሰው ሀይልን ልታበረክት ይገባል ብለዋል፡፡

እንዲሁም ቀደም ብሎ በአቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ ብቻ ተገድቦ የነበረውን ስልጠና ለወጣቶች እና ለታዳጊ ተማሪዎች በትምህርት ቤቶች በመስጠት ግንዛቤውን  ለማስፋት የጋራ ስራ መስራት ይገባናል ብለዋል።

የሀሳቡ ባለቤት እና የኢትዮጵያ ኤሮ ክለብ መስራች አቶ ዮናታን መንክር በበኩላቸው÷ ከልጅነት ጀምሮ የበረራና የኤሮስፔስ ፍቅር ያላቸውን ታዳጊዎች በእውቀት በማበልፀግ ለዘርፉ ብቁ ማድረግ ህፃናት ህልማቸውን እንዲያገኙ ማገዝ የትግበራው ዋና አላማ መሆኑን ጠቁመዋል።

በስምምነቱ መሰረት የአቪዬሽን እውቀትና ግንዛቤ በመደበኛ ት/ቤቶች፣ በኮሌጆች፣ በቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛዎች እና በዩኒቨርሲቲዎች ይሰጣል ።

በመታገስ አየልኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.