በቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ብሔራዊ የጥራት ማረጋገጥ ፕሮግራም ሊተገበር ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ብሔራዊ የአገልግሎት ጥራት ማረጋገጥ ፕሮግራም በቅርቡ እንደሚተገበር የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ጎብኚዎችን በሚያስተናግዱ እንደ ሆቴልና መሰል ተቋማት ጥራት እንዳይኖር ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል በዘርፉ ብቁ የሰው ኃይል አለመገንባት፣ የስልጠና እና የልኅቀት ተቋማት ማነስ መሆኑ ይነሳል፡፡
ችግሩን ለመፍታትም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የስርዓተ ትምህርት ማሻሻያ የማድረግ እና ደረጃውን የጠበቀ ወጥ አሰራር የመፍጠር እና የልኅቀት ማዕከል ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ አስታውቀዋል፡፡
አስጎብኚ ድርጅቶችን ጨምሮ ለቱሪዝም ዘርፍ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የብቃት ማረጋገጥ ስራ እየተተገበረ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በዚህም ባለኮከብ ሆቴሎች የሚሰጡት የአገልግሎት ጥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ አቻ ሆቴሎች ጋር ተመሳሳይ መሆን እንደሚገባው ነው ያመላከቱት፡፡
የአገልግሎት ጥራትን በሁሉም አካባቢ ወጥነት ባለው መልኩ ለማሻሻልም ዓለም አቀፍ መስፈርትን ያሟላ ብሔራዊ የአገልግሎት ጥራት ማረጋገጥ ፕሮግራም በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
ይህም የአገልግሎት ጥራትን ከማስጠበቅ ባሻገር የጥራት መጓደልን የሚጠየፍ ማህበረሰብ ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ዩኔስኮ ዕውቅና ለሰጣቸውም ሆነ ገና ላልተመዘገቡ ቅርሶች ጥበቃ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በቅርስ ጥገና ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ትልቅ ተግዳሮት መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሯ÷ ችግሩን ለመቅረፍ የስልጠና አማራጮችን ማስፋት ላይ ትኩረት መደረጉንም ተናግረዋል።
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡ FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!