Fana: At a Speed of Life!

ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የምክክር ሂደቶችን ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ ነው -መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሀገራዊ ምክክር ሂደቶችን ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የሀገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነሩ መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ገለጹ።

በበርካታ ክልሎች ሲካሄድ የቆየው የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች ልየታ በመጪው ሳምንት በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

ዋና ኮሚሽነሩ መስፍን አርዓያ (ዶ/ር)÷የሀገራዊ ምክክር ሂደቶችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎችም የሀገራዊ ምክክሩ ሂደቶች ለማከናወን ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።

ነፍጥ ያነሱ ወገኖች በሰላማዊ መንገድ ወደ ምክክሩ እንዲመጡ መንግስት ለሰላማዊ አማራጭ ቅድሚያ ሰጥቶ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ረገድ የበለጠ መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ እንደ ገለልተኛ ተቋም ከሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ መስራት እንደሚፈልግ ገልጸው÷ ሁሉም ፓርቲዎች ወደ ምክክር እንዲገቡ መንግስት የበለጠ ማገዝ እንዳለበት አንስተዋል።

ኮሚሽኑ በሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ አፋር፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ሀረሪ፣ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች የተሳታፊ ልየታ ማካሄዱን አስታውሰዋል።

በመጭው ሳምንት በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች የተሳታፊዎች ልየታ እንደሚቀጥልም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በፓሲፊክ እና እስያ እንዲሁም በአውሮፓ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በበይነ መረብ ውይይት መደረጉንም ነው ዋና ኮሚሽነሩ የገለጹት፡፡

ከሰሞኑም በአሜሪካ ከሚኖሩ ዳያስፖራ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ውይይቱ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.