Fana: At a Speed of Life!

የወንጪ-ደንዲ ኢኮቱሪዝም መደመር በተግባር የታየበትና በአጭር ጊዜ ትልቅ ስራ መስራት እንደሚቻል የተረጋገጠበት ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የወንጪ-ደንዲ ኢኮቱሪዝም ፕሮጀክት መደመር በተግባር የታየበትና በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ ስራ መስራት እንደሚቻል የተረጋገጠበት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወንጪ-ደንዲ ኢኮቱሪዝም ፕሮጀክትን ዛሬ ሲመርቁ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ፕሮጀክቱ ከተለያየ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተሰባሰበ ሀብት፣ ከተለያዩ አካባቢዎች በመጡ ባለሙያዎች እና የፕሮጀክት አስተባባሪዎች የተገነባና መደመር በተግባር የታየበት ነው ብለዋል።

ከወንጪ አካባቢ የወጡ በርካታ ጀግኖች የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅና ሉዓላዊነት ለማስከበር ትልቅ ውለታ መዋላቸውን አስታውሰዋል።

መደመር በጋራ ተያይዞ ማደግ መሆኑን ጠቁመው የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ መደመር ወሳኝ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ወንጪንና አካባቢውን በልማት ማስተሳሰር የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።

የወንጪ-ደንዲ ኢኮቱሪዝም ፕሮጀክት የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን ያቀፈ በመሆኑ ባለሀብቶች በቀጣይ ለሚሰሩት ስራ የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።

የወንጪ-ደንዲ ኢኮቱሪዝም ፕሮጀክት ስራን ጀምረን በአጭር ጊዜ ውስጥ በጥራት ማከናወን እንደምንችል ማሳያ ነው ብለዋል።

ይህ ፕሮጀክት ጅምር ስራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ አምቦን፣ ወንጪ-ደንዲ ሀይቅን፣ ወሊሶን አንድ ላይ የሚያስተሳስር ትልቅ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ለዚህም ባለሀብቶች በስፋት በኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ የክልሉ መንግስት በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

የወንጪ አካባቢ ማህበረሰብ የአካባቢውን ተፈጥሮ ጠብቆ እንዳቆየ አሁንም ይህንኑ ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፈዋል።

በባህሉ እንግዳ ተቀባይ የሆነው ህዝብ ወንጪ-ደንዲን ለመጎብኘት የሚመጡ እንግዶችን ተንከባክቦ አስተናግዶ በደስታ እንዲመለሱ በማድረግ የጎብኚዎችን ቀልብ መሳብና የተሻለ ገቢ የሚያገኝበትን መንገድ ማመቻቸት ይኖርበታል ብለዋል።

በተፈጥሮ በተቸረን ሀብት ላይ ጠንክረን በመስራት ብልጽግናችንን ማረጋገጥ ይገባናል ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.