ወንጪ-ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት የቱሪስት ከተማ የመገንባት ራዕይ ያለው ነው – አብርሃም በላይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የወንጪ-ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት የቱሪስት ከተማ የመገንባት ሰፊ ራዕይ ያለው ትልቅ ሀገራዊ የልማት አሻራ መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትሩና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ገለጹ።
የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አካል የሆነው የወንጪ-ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ዛሬ በይፋ ተመርቋል።
የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) እንዳሉት፥ ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ነዋሪ የመሰረተ ልማት፣ የስራ እድልና ሌሎች በርካታ ጥቅሞችን ይዞ መጥቷል።
በግንባታ ሂደት ብቻ ከ10 ሺህ ለሚበልጡ የአካባቢው ነዋሪዎች የስራ ዕድል የፈጠረ መሆኑንም አብራርተዋል።
ፕሮጀክቱ ከቱሪስት መዳረሻነት ባሻገር ለአካባቢው የማያቋረጥ የስራ እድልና ልማት ማስገኘቱን እንደሚቀጥል ጠቁመው፤ ለአብነትም በ22 ማህበራት ለተደራጁ ከ560 የሚበልጡ ወጣቶች በተለያዩ ዘርፎች የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ መሰራቱን ጠቁመዋል።
የአካባቢው ነዋሪ ስራና ሀገሩን ወዳድ በመሆኑ በፕሮጀክቱ ስራ እውቀቱንና ያለውን ሃብት ያለስስት መስጠቱን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ከወሊሶ አምቦ፣ ከወንጪ ደንዲ፣ ከደንዲ አስጎሪ ሰፊ የሆነ ቦታ ላይ በምዕራፍ ተከፋፍሎ እንዲገነባ የተቀረጸ ሰፊ ራዕይ ያለው ትልቅ ሀገራዊ የልማት አሻራ መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ የቱሪስት ከተማን የመገንባት ሰፊ ሀገራዊ ራዕይ ያለው መሆኑን አብርሃም በላይ (ዶ/ር) መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የወንጪ-ደንዲ ፕሮጀክት የመደመርና የአብሮነት ትርጉም በተግባር የተገለጠበት ነው ብለዋል።