114 የዓይን ብሌኖች ተዘጋጅተው ለንቅለ ተከላ እንዲውሉ ለሕክምና ተቋማት መሰራጨታቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ 114 የዓይን ብሌኖችን በማሰባሰብ እና በማዘጋጀት ለንቅለ ተከላ እንዲውሉ ለሕክምና ተቋማት ማሠራጨቱን የኢትዮጵያ ደም እና ኅብረ-ኅዋስ ባንክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡
129 የዓይን ብሌኖችን በማሰባሰብ፣ በማዘጋጀት እና ለንቅለ ተከላ ዝግጁ በማድረግ ለሕክምና ተቋማት ለማሠራጨት ታቅዶ 114 ማሳካት መቻሉን የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሐብታሙ ታዬ ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም 200 በጎ ፈቃደኞች ከኅልፈት በኋላ የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡
በ2015 ዓ.ም ዓመቱን ሙሉ የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል የገቡት ሰዎች 190 መሆናቸውን አስታውሰው÷ ዘንድሮ በግማሽ ዓመት ብቻ 200 ሰዎች ቃል መግባታቸው የሕብረተሰቡ ግንዛቤ እያደገ መምጣቱን ያሳያል ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ አሁንም በርካታ ወገኖች በዓይን ብሌን ጠባሳ ምክንያት አይነ ስውር እንደሆኑ ጠቅሰው፤ ሕብረተሰቡ ከኅልፈት በኋላ የዓይን ብሌኑን እንዲለግሥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው