የወንጪ-ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም ዘርፈ-ብዙ ጥቅም ማምጣቱ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የወንጪ-ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት ከቱሪዝም ሴክተሩ ባሻገር ዘርፈ-ብዙ ጥቅም ይዞ መምጣቱን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር ገለፁ፡፡
የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አካል የሆነው የወንጪ-ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ትናንት በይፋ ተመርቋል።
ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ፕሮጀክቱን በማስመልከት ባደረጉት ንግግር÷ ፕሮጀክቱ ከቱሪዝም ባሻገር የአካባቢው ማኅበረሰብ ከቦታው ሳይፈናቀል፤ በማስጎብኘትም ሆነ በሌሎች ዘርፎች በመሳተፍ የተሻለ ኑሮ የሚያገኝበት ዕድል ፈጥሯል ብለዋል፡፡
ሰው ተኮር የሆኑ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸው ጠቁመው÷ የወንጪ-ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክትም አንዱ ማሳያ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ፕሮጀክቱ መሰል የልማት ሥራዎች ሲሠሩ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ባገናዘበ መልኩ መሆን እንዲችሉ ትልቅ ዕድልና ትምህርት መፍጠሩንም ጠቅሰዋል፡፡
በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ለረዥም ዓመታት በመምህርነት ያገለገሉት ዓለማየሁ ገብረማርያም (ፕ/ር) በበኩላቸው÷ የወንጪ ደንዲ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ በኢኮ-ቱሪዝም ያከናወነችውን ስኬት በተግባር ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አካባቢውን፣ ባሕሉንና የሕዝቡን አኗኗር በማሳየትና በማቀናጀት በዘርፉ በአፍሪካ በተምሳሌትነት ሊጠቀስ የሚችል ስለመሆኑ አመላክተዋል፡፡