በአማራ ክልል ለፀጥታ አመራሮች ስልጠና መሠጠት ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ለከፍተኛና መካከለኛ የፀጥታ አመራር አባላት የአቅም ግንባታ ስልጠና መሠጠት ተጀምሯል፡፡
ስልጠናው በዛሬው ዕለት በጎንደር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደሴ እና ደብረ ብርሃን ከተሞች የተጀመረ ሲሆን÷ እስከ ጥር 13 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚቆይ ተገልጿል፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ የሕዝብ ግንኙነትና አደረጃጀት አማካሪ ይርጋ ሲሳይ በጎንደር የስልጠና ማዕከል ባደረጉት ንግግር÷ የፀጥታ መዋቅሩ የጋራ አመለካከትና አቅጣጫ በመያዝ በክልሉ ለዘላቂ ሰላም መስፈን በትኩረት ሊሠራ ይገባል ብለዋል።
የፀጥታ መዋቅሩ የአመለካከትና አስተሳሰብ ዝንፈቶችን፣ የጽንፈኝነት አስተሳሰብና ተግባርን አጥብቆ ሊታገል እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥና የክልሉ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌ/ጄ ብርሃኑ በቀለ በበኩላቸው÷ የፀጥታ መዋቅሩ ለሀገሩና ለሕግ ልዕልና ሥርዓት መከበር በመቆም ኃላፊነቱን በብቃት እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
በተመሳሳይ ክልሉ ከፀጥታ ችግር ነጻ ሆኖ የተጀመሩ የልማት ተግባራት በአግባቡ እንዲከናወኑ የፀጥታ አካላት ጉልህ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የገለፁት ደግሞ በደብረ ማርቆስ ስልጠና ማዕከል የተገኙት የምሥራቅ ዕዝ ዋና አዛዥና የጎጃም ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌ/ጄ መሐመድ ተሰማ ናቸው፡፡
የክልሉ ኮማንድ ፖስት ምክትል ሰብሳቢና የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ደሳለኝ ጣሰው በበኩላቸው÷ የተረጋጋ ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ ሕዝባዊነትን የተላበሰና ተልዕኮውን በአግባቡ የሚወጣ የጸጥታ ኃይል መገንባት የግድ መሆኑን ጠቁመው ስልጠናው ይህን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በደሴ የስልጠና ማዕከል የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት÷ አመራሩና የፀጥታ መዋቅሩ የጋራ አመለካከትና ሐሳብ ይዞ የክልሉን ሰላም ዘላቂ እንዲያደርግ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የምስራቅ አማራ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌ/ጄ አሰፋ ቸኮል÷ የፀጥታ መዋቅሩ ከሕዝብ ጋር ተቀናጅቶ የኢትዮጵያን ሰላምና ሉዓላዊነት በማስጠበቅ ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
እንዲሁም በደብረ ብርሃን የስልጠና ማዕከል የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አህመዲን መሃመድ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ ስልጠናው በየደረጃው ያለውን የጸጥታ አመራር እና አባሉን በአስተሣሠብና በተግባር ለማናበብ ያለመ ነው፡፡
አሁን ለገጠመን ዓለም አቀፋዊና ውስጣዊ ፈተና ጽናትን፣ ቁርጠኝነትን እልህ መላበስ እንዲሁም በመተማመን በቁርጠኝነት መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
ዓለም አቀፍ ስጋትን አሉታዊ ፍላጎትን ለመግታት እንዲሁም ውስጣዊ ዝግጅትን ለማጠናከር ስልጠናው አቅም እንደሚሆን ተጠቅሷል፡፡
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡ (FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!