በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚገኙ የተመድ ሰላም አስከባሪዎች ሀገሪቱን ለቀው መውጣት ጀመሩ
አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላም አስከባሪዎች ሀገሪቱን ለቀው መውጣት መጀመራቸውን አስታወቀች፡፡
ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የመንግስታቱ ድርጅት ሰላም አስከባሪ ሃይል ለሦስት አስርት ዓመታት ዜጎቼን ሲያሰቃዩብኝ ነበር ካለቻቸው ታጣቂ ቡድኖች ሊጠብቅልኝ አልቻለም ማለቷ ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎም ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተመድ ሰላም አስከባሪዎች ሀገሪቷን ለቀው እንዲወጡ ጥሪ አቅርባ ነበር፡፡
አሁን ላይም የተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪ ሃይል ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መውጣት መጀመሩን የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
በአንጻሩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በምስራቃዊው የሀገሪቱ ክፍል ባለው አለመረጋጋት ስጋት እንዳለው መጠቆሙን ቲ አርቲ ዘግቧል፡፡
የተመድ የሰላም አስከባሪ ሃይል 13 ሺህ 500 ወታደሮችን እና 2 ሺህ ፖሊሶችን በሦስቱ የሀገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል ግዛቶች አሰማርቶ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡