Fana: At a Speed of Life!

ሕብረተሰቡ የወባ በሽታ መከላከያ መንገዶችን በአግባቡ እንዲተገብር ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለወባ በሽታ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የመከላከያ መንገዶችን በአግባቡ በመተግበር ራሳቸውን እንዲጠብቁ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አሳሰበ።

በወላይታ ዞን ኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ በተለይም ሼላ ሳዴ ቀበሌ የወባ በሽታ መስፋፋቱን በቢሮው የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለሙያ አስራት ቦሻ ተናግረዋል፡፡

በወረዳው የወባ በሽታ ታማሚዎች ቁጥር መጨመሩን ጠቅሰው÷ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የቤት ለቤት አሰሳ በማድረግ የመድኃኒትና የሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልፀዋል።

የወላይታ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ፀጋዬ ኤካ እንዳሉት÷ ለወባ ተጋላጭ ከሆኑት አካባቢዎች  መካከል በሆነችው ሼላ ሳዴ ቀበሌ በተለየ ሁኔታ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ማሻቀቡን አስታውቀዋል፡፡

በቀበሌው ከ869 ሰዎች የደም ናሙና ተወስዶ 680ዎቹ በበሽታው መያዛቸውም ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

ሕብረተሰቡ በሽታውን ለመከላከል ማድረግ የሚጠበቅበትን የመከላከያ ስልቶች በአግባቡ አለማከናወኑ ለበሽታው ስርጭት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ነው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት፡፡

የኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሕዝቅኤል ሜንታ በበኩላቸው÷ ባለፉት ቀናት በተደረገ ምርመራ ከ2 ሺህ 8 መቶ ሰዎች መካከል 1 ሺህ 5 መቶ 83 ያህሉ በበሽታው ተይዘዋል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ወቅቱ የወባ በሽታ ሥርጭት የሚበረታበት በመሆኑ ሕብረተሰቡ ውኃ ያቆሩ ሥፍራዎች በማፋሰስ፣ በማዳፈንና አጎበርን በአግባቡ በመጠቀም ራሱንና ቤተሰቡን ከወባ በሽታ እንዲከላከል ኃላፊዎቹ አሳስበዋል፡፡

በመለሰ ታደለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.