በኦሮሚያ ክልል 3 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር ላይ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ለማከናወን ታቅዷል
አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል 3 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ለማከናወን መታቀዱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ እንደ ትውልድ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀማችን ሚዛናዊ የመሆን ግዴታ አለበት ብለዋል፡፡
በተያዘው ዓመት ያለፉትን ዓመታት ተሞክሮዎች በመቀመር ለውጡን የበለጠ መሬት ለማስያዝ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዚሁ መሠረት በዜግነት አገልግሎትና በመንግስት መዋቅር እስከ 3 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት፣ የአፈር እና የውሃ ጥበቃ ስራ ለማከናወን መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡
ይህም እስከ 10 ሚሊየን የማህበረሰብ አባላት በማንቀሳቀስ እንደሚሰራ ጠቁመው÷ ሥራው ወደ ጥሬ ገንዘብ ሲቀየርም የ10 ቢሊየን ብር ዋጋ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
በእስካሁኑ ስኬት የተሳተፉትን የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የግብርና ባለሙያዎች እና በየደረጃው ያሉ የአመራር አካላትን አመስግነዋል፡፡
በቅርቡ በይፋ ለሚጀመረው የዘንድሮው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ዘመቻ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ዝግጅት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡