ከ287 ሚሊየን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ
አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ287 ሚሊየን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዙን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ ከታሕሳስ 26 እስከ ጥር 2 ቀን 2016 ዓ.ም ባደረገው ክትትል ነው 140 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር የገቢ እና 146 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር የወጪ ኮንትሮንድ እቃዎች የያዘው፡፡
ከተያዙት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሃኒት፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣የመኪና መለዋወጫ፣ የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡
ኮንትሮባንዱን ሲያዘዋውሩ የተገኙ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች እና ስምንት ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡
በተጠቀሰው ጊዜ የገቢ እና የወጪ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር አዲስ አበባ ኤርፖርት፣ ድሬድዋ እና ሞያሌ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዙ ተጠቁሟል፡፡