በጋምቤላ ክልል የኢንዱስትሪ አምራቾች ምቹ ሁኔታ እንዲያገኙ በትኩረት ይሰራል – አቶ ኡሞድ ኡጅሉ
አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ያሉ የኢንዱስትሪ አምራቾች ምቹ ሁኔታ እንዲያገኙ በትኩረት እንሰራለን ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ፡፡
በአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ላይ ከሚመለከታቸው ከፍተኛ አመራሮች ጋር በጋምቤላ ከተማ ምክክር እየተካሄደ ነው፡፡
አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በውይይቱ እንደገለጹት÷በክልሉ በተለያዩ ዘርፎች የተሻሻሉ የልማት ፖሊሲዎችን ተግባራዊ በማድረግ መጠነ ሰፊ የማሻሻያ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡
የኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዲያድግ በክልሉ ያሉ የኢንዱስትሪ አምራቾች ምቹ ሁኔታ እንዲያገኙ እንሰራለንም ነው ያሉት፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ በበኩላቸው÷በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታትና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግሩን ለማሳካት የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልፀዋል፡፡
የዘርፉን ዕድገት ለማፋጠን የኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄ መጀመሩንና ተስፋ ሰጪ ለውጥ እየታዬ መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ አምቢሳ ያደታ እንደገለፁት÷ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ የአምራች ኢንዱስትሪ ማዕከል እንድትሆን ለማስቻል በክልሉ ዘርፉን ለማሳደግ በትኩረት ይሰራል።
የአምራች ኢንዱስትሪ ልማትና የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተፈለገው ልክ ውጤት ማምጣት እንዲችል ለዘርፉ እድገት ማነቆ የሆኑ ጉዳዮችን በዝርዝር መፍታት ይጠበቅብናል ማለታውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡