በጅማ ከተማ በደረሰ የእሳት አደጋ የ2 ሰዎች ህይወት አለፈ
አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማ ዛሬ ረፋድ ላይ 4:00 ሰዓት ገደማ በደረሰ የእሳት አደጋ የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።
በከተማው ቦሬ በተባለ አካባቢ በደረሰ የእሳት አደጋ ህይወታቸው ካለፈው ሁለት ሰዎች በተጨማሪ ሁለት ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት እንዲሁም አራት ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት መድረሱ ተገልጿል፡፡
የጅማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የኮሙኒኬሽንና ሚዲያ ዲቪዥን ሃላፊ ምክትል ኮማንደር ገዛኸኝ አጉቸው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት÷ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በጅማ ዩኒቨርሲቲ ህክምና ማዕከልና በሸነን ጊቤ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ነው።
የአደጋው መንስኤና በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት መጠን እየተጣራ መሆኑንም ምክትል ኮማንደሩ ገልፀዋል።
በሙክታር ጠሃ