የጨጓራ ሕመም
አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጨጓራ ሕመም ከተለመደው የጨጓራ አሲድ መጠን በላይ መከሰትን ተከትሎ ከሚመጣው ከምግብ በኋላ ምቾት ማጣት ስሜት ውጪ እንደመነሻውና የእድሜ ደረጃ የተለያዩ መገለጫዎች አሉት፡፡
የጉበት፣ የጨጓራ እና የአንጀት ሕክምና ስፒሻሊስት ፕሮፌሰር አባተ በኒ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፥ በኢንፌክሽን ወይም በአለርጂ የሚመጡ የጨጓራ መቁሰል፣ መድማት፣ እብጠት፣ እጢ ብሎም የጨጓራ ካንሰር ሁሉ በየደረጃው የጨጓራ ሕመሞች ናቸው፡፡
ህጻናት ላይ የተለመደው ከኢንፌክሽን እና ከምግብ አለመስማማት ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል፡፡
ከወጣቶችና ጎልማሶች ጋር በተያያዘ ደግሞ ኢንፌክሽን፣ ምግብ፣ ሱስ፣ የካንሰር እና ሌሎች መድኃኒቶች ጨጓራ እና አንጀትን ሊያቆስሉ እንደሚችሉም ነው የተናገሩት፡፡
እድሜ እየገፋ ሲመጣ ደግሞ ከዚህ በተጨማሪ ካንሰርን ሊያስከትል ይችላልም ብለዋል፡፡
የጨጓራ ሕመም እንደየደረጃው ምልክቶቹ እንደሚለያዩ ያነሱት ፕሮፌሰር አባተ፥ የሆድ ህመም፣ የቁስለትና የማቃጠል ስሜት፣ የሆድ መነፋት፣ የማቅለሽለሽና ማስመለስ ስሜቶች አብዛኛውን ጊዜ የሚታዩ ምልክቶች እንደሆኑ አንስተዋል፡፡
ቀላል ጨጓራ በሽታ የሚባለው ቁስለት፣ እብጠት፣ ጥበት የሌለባቸው ሲሆኑ፥ ህመም የሚያባብሱ ነገሮችን በማስወገድ፣ አመጋገብን በማስተካከል መቆጣጠር እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
ከባዱ ደግሞ የመቁሰል፣ የማበጥ እስከ ካንሰር የሚደርስ የጨጓራ ሕመም ነው፡፡
ሆኖም ያለበትን ደረጃ ለማወቅ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል ነው የተባለው፡፡
የሕክምና ባለሙያው ፕሮፌሰር አባተ እንዳሉት፥ አንዳንዴ ስሜቱ ወይም ምልክቱ ቀላል ሆኖ በምርመራ ጊዜ ግን አስደንጋጭ ውጤት ይገኛል፤ በሌላ በኩል ሕመሙ (ስቃዩ) ከፍተኛ ሆኖ ምርመራ ሲደረግ በቀላሉ ሊድን የሚችል ሆኖ ይገኛል፡፡
በዚህም ከሁለት ሣምንት በላይ የቆየ ቀላልም ሆነ ከባድ የሕመም ስሜት ሲሰማዎ ወደ ሕክምና መሄድና ተገቢውን ምርመራ ማድረግ እንደሚያስፈልግ መክረዋል፡፡
ከፍተኛ ደረጃ እንደአብነት መድማት ካጋጠመዎ የሚደማው እንዲያቆም የማድረግ ፤ እብጠት ካለም ቀርፎ የማውጣት ሕክምና በኢንዶስኮፒ ይሰጣልም ነው ያሉት፡፡
የቀዶ ሕክምና የሚያስፈልገው የተበሳና ጥበት ካለ እንዲሁም እጢ ሆኖ ስሩ ሰፊና በኢንዶስኮፒ መታከም የማይችል ሲሆን ነው ብለዋል ፕሮፌሰር አባተ፡፡