ማኅበሩ በሰሜኑ ጦርነት ለተጎዱ ጤና ተቋማት 16 ሚሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማሕበር በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው ጤና ተቋማት 16 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የሕክምና ቁሣቁስ ድጋፍ አደረገ።
የማኅበሩ ዳሬክተር ዓለማየሁ መኮንን÷ በሰሜን እና በደቡብ ወሎ ዞኖች ለሚገኙ 10 ወረዳዎች ድጋፉ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ድጋፉ ከፓካርድ ፋውንዴሽን በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በወረዳዎቹ ለሚተገበረው የሥነ-ተዋልዶ ፕሮጀክት የጤና ተቋማት ማሻሻያ እንደሚውልም ተመልክቷል፡፡
ከአማራ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር 39 ጤና ጣቢያዎች እና 70 ጤና ኬላዎችን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠሩም ነው የተገለጸው፡፡
ከእያንዳንዱ ዞን አምሥት ወረዳዎች በጥናት የተለዩ ሲሆን በደረሰባቸው የጉዳት መጠን መሰረት ቅድሚያ እንደሚሰጥም ነው የተጠቆመው፡፡
የሰሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ብርሃን ኃይሌ÷ ድጋፉ መሠረታዊ የጤና ተቋማትን ችግር የሚፈታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታቸው በለጠ በበኩላቸው÷ የጤና ተቋማት የተሻለ የሕክምና አገልግሎት መሥጠት የሚያስችላቸው ድጋፍ መደረጉን ገልጸው፤ ምስጋና አቅርበዋል።
በአለባቸው አባተ