የምርቶችን ዓለም አቀፍ ጥራት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት አግዛለሁ- ዓለም ባንክ
አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የምርቶችን ዓለም አቀፍ ጥራት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በቴክኖሎጂ እና በሰው ኃይል እንደሚደግፍ ዓለም ባንክ አስታወቀ፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ በዓለም ባንክ የኢትዮጵያን ጨምሮ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ዋና ዳይሬክተር ኦስማን ዲዮን ጋር ተወያይተዋል፡፡
አቶ ገብረመስቀል በውይይቱ ላይ በግሉ ዘርፍ ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶች ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃቸውን አሟልተው እንዲወጡ ለማስቻል በብሄራዊ የጥራት ደረጃ መሰረተ ልማት ላይ የሚሰሩ ስራዎች ከፍተኛ ቦታ እንዳላቸው ጠቅሰዋል፡፡
ኦስማን ዲዮን በበኩላቸው÷ መንግሥት ለጥራት መሰረተ ልማት የሰጠውን ትኩረት ለማገዝ የቴክኖሎጂ፣ የሰው ኃይል እና መሰል ድጋፎችን እናደርጋለን ማለታቸውን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
ሚኒስቴሩ በጥራት መሰረተ ልማት ላይ እያከናወናቸው የሚገኙ ሥራዎችንም ተምልክተዋል፡፡