Fana: At a Speed of Life!

ለ2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን የቱሪስት መስህቦችን ለማስጎብኘት ዝግጅት ማድረጉን የአማራ ክልል ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በውጭ ለሚኖሩ 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በአማራ ክልል የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማስጎብኘት ዝግጅት ማድረጉን የክልሉ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ሃላፊ አቶ ጣሂር መሃመድ እንደገለጹት÷ በውጭ የሚኖሩ 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን እንዲጎበኙ የቀረበው ጥሪ የክልሉን ቱሪዝም ለማነቃቃት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጋል፡፡

በተለይም በአማራ ክልል በጥር ወር የሚከበሩ የተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላት መኖራቸው ጥሪውን ልዩ ያደርገዋል ነው ያሉት፡፡

ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ኢትዮጵያውያኑ በአማራ ክልል የሚኖራቸውን ቆይታ ስኬታማ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ዝግጅት መደረጉን ሃላፊው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

በተለይም የማይዳሰሱና የሚዳሰሱ ቅርሶችን እንዲሁም የቱሪስት መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ ከአስጎብኚ ማህበራት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሰራቱን ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም የአማራ ሕዝብን ባህል፣ የአለባበስ ሥርዓት፣ ባህላዊ ምግቦች፣ ባሕላዊ ጭፈራዎች እና ሌሎች እሴቶችን ለማስተዋወቅ የተለያዩ ሁነቶች መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ ሆቴሎች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ኢትዮጵያውያኑን ለማስተናገድ ዝግጅታቸውን እንዳጠናቀቁና በአገልገሎቶች ላይ ቅናሽ እንደሚያደርጉም አስገንዝበዋል፡፡

የጥምቀት በዓል በጎንደርና ምንጃር ሸንኮራ፣ የአገው ፈረሰኞች ማህበር በዓል በእንጅባራ፣ የጊዮን በዓል በሰከላ እንዲሁም ጥርን በባህርዳር በአማራ ክልል በቀጣይ በድምቀት የሚከበሩ በዓላት መሆናቸውንም አመላክተዋል፡፡

ስለሆነም በውጭ የሚኖሩ 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን የክልሉን ባህል እና እሴት እንዲሁም ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ መስህቦችን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.