የዓድዋ ድል መታሰቢያ ውስጥ የሚቀመጡ ቅርሶችን ማሰባሰብ ጀምረናል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በታላቁ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ውስጥ የሚቀመጡ በግለሰቦችና በተቋማት እጅ የነበሩ ከጦርነቱ፣ ከጀግንነትና ከድሉ ጋር የሚያያዙ ቅርሶችን ማሰባሰብ ጀምረናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷በዛሬው ዕለት የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን፣ የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር እንዲሁም የአዲስ አበባ ሙዚየም ቅርሶችን እንዳስረከቡ ገልጸዋል፡፡
ቅርሶቹን በክብር ያስረከቡትን አመስግነው÷ ሌሎችም የእነሱን ዓርዓያ በመከተል በእጃቸው ያሉ ከጦርነቱ፣ ከጀግንነት እና ከድሉ ጋር የሚያያዙ ቅርሶችን እንዲያስረክቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ቅርሶች በየቦታው ተበታትነው በአግባቡ ሳይታወቁ እንዳይቀሩ፣ ትውልድ እዲያውቃቸው፣ እንዲማርባቸው፣ ጎልተው እንዲታዩና ከፍታቸውን በሚመጥነው ታላቁን የዓድዋ ድል መታሰቢያ ውስጥ ታሪካዊ ይዘታቸውን በጠበቀ መልኩ እንዲቀመጡና ለዕይታ እንዲቀርቡም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡