የመውጫ ፈተና ድጋሜ ተፈታኞች ከጥር 27 ጀምሮ ፈተናውን እንደሚወስዱ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016 ዓ.ም አጋማሽ ላይ የየሂኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናን በድጋሜ ለመፈተን በመጠባበቅ ላይ ላሉ ተፈታኞች ፈተናው ከጥር 27 እስከ የካቲት 1 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚሰጥ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ከ2015 የትምህርት ዘመን ጀምሮ በሁሉም በቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞች ለእጩ ተመራቂ ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት የመውጫ ፈተና እየተሰጠ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በዚህም ሚኒስቴሩ የመውጫ ፈተና በድጋሜ ለሚፈተኑ አመልካቾች እንዳስታወቀው÷የመውጫ ፈተናን በድጋሜ ለመፈተን በመጠባበቅ ላይ ያሉ ተፈታኞች ፈተናው ከጥር 27 እስከ የካቲት 1 ቀን 2016 ዓ.ም የሚሰጥ እንደሆነ ገልጿል፡፡
በሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም የመውጫ ፈተናውን ተፈትነው ያላለፉ እና ከጥር 27 – የካቲት 1ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ የመውጫ ፈተናውን በድጋሜ ለመውሰድ በመጠባበቅ ላይ ያሉ ተፈታኞች ምዝገባ የሚያካሂዱትና የመፈተኛ ተቋም የሚመርጡት ከታች በተገለጸው ማስፈንጠሪያ መሆኑንም ገልጿል፡፡
(https://exam.ethernet.edu.et)
እንዲሁም ከጥር 8 እስከ ጥር 15 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ የምዝገባ ክፍያ 500 ብር በቴሌ ብር ብቻ በመክፈል መመዝገብ እንደሚችሉም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
አመልካቾች ተጨማሪ ድጋፍ የሚፈልጉ ከሆነ በስልክ ቁጥር +251 118 13 21 76 ወይም በኢሜይል registration@ethernet.edu.et በኩል ድጋፍ ማግኘት እንደሚችሉ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ የመውጫ ፈተና የሚፈተኑ እጩ ተመራቂዎች ምዝገባ የሚያካሂዱት እና የአገልግሎት ክፍያ የሚፈፅሙት በተቋማቸው በኩል መሆኑንም አሳስቧል፡፡
አስፈላጊ የመፈተኛ መረጃዎችም በተቋማት በኩል ለተፈታኞች የሚደርሳቸው መሆኑን ሚኒስቴሩ ጨምሮ አስታውቋል፡፡