ከ5 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ጂቡቲ ወደብ መድረሱ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ2016/17 የምርት ዘመን ከውጭ ከተገዛው የአፈር ማዳበሪያ መጠን ውስጥ በ11 ዙሮች 5 ሚሊየን 859 ሺህ 403 ኩንታል ጂቡቲ ወደብ መድረሱን የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ገለጸ፡፡
960 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ የጫነች ግዙፍ መርከብ ደግሞ ዛሬ ወደብ መድረሷን ገልጿል፡፡
ከዛሬ ጀምሮ በቀጣይ በሦስት መርከቦች 1 ሚሊየን 822 ሺህ 500 ኩንታል ተጨማሪ የአፈር ማዳበሪያ ጂቡቲ ወደብ እንደሚደርስ ይጠበቃል መባሉን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር በየዓመቱ እያጠና በሚያቀርበው የሀገሪቱ የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት መሰረት ኮርፖሬሽኑ ከተቋቋመበት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ዓለም አቀፍ ጨረታ እያወጣ የማዳበሪያ ግዥ እየፈጸመ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡