በሙስና ወንጀል የተጠረጠረው የፍርድ ቤት ዳኛ ላይ ለተጨማሪ ማጣሪያ 14 ቀን ተፈቀደ
አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሙስና ወንጀል የተጠረጠረው የፍርድ ቤት ዳኛ ላይ ለተጨማሪ ማጣሪያ 14 ቀን መፈቀዱ ተገለጸ፡፡
ለፖሊስ የተጨማሪ የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ የፈቀደው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው።
ተጠርጣሪው የአዲስ አበባ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ዳኛ እና የኢንስፔክሽን ኃላፊ የሆነው ተስፋዬ ደረጄ ረጋሳ የሚባል ሲሆን ÷ የአዲስ አበባ ፖሊስ መርማሪ የተጠረጠረበት መነሻን ዛሬ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አብራርቷል።
በዚህም የአቢሲኒያ ባንክ መስቀል ፍላወር ቅርጫፍ ስራ አስኪያጅ የነበረ እና በሙስና ወንጀል የተከሰሰ ሀብተማርያም ገ/መስቀል የተባለ ግለሰብ መስከረም 7 ቀን 2014 ዓ.ም በፌደራል ፖሊስ ቢሮ በእስር ላይ በነበረበት ወቅት ሚካኤል ታደሰ በተባለ ግለሰብ አማካኝነት ተጠርጣሪው በእስር ቤት በአካል በመሄድ ከተዋወቀው በኋላ ዳኛ መሆኑን በመግለጽ ጉዳዩን እንደሚያስጨርስለት እና መዝገቡን የሚያዩለት ዳኞችን ስም ደውለህ ንገረኝ በማለት ስልክ ቁጥሩን ሰጥቶት መሄዱን ፖሊስ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አብራርቷል።
ከዚህም በኋላ የግል ተበዳይን ጉዳይ የያዙት ዳኞች የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሙስና ጉዳይ ችሎት ዳኞች መሆናቸውን ስማቸውንም ከግል ተበዳይ ጠይቆ ከተረዳ በኋላ ሀለቱ ዳኞች በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አብረውት የተማሩ መሆናቸውንና እንደሚያውቃቸው በመጥቀስ ፤ አንደኛውን ዳኛ ደግሞ የስራ ባልደረባዬ አለቃዬ ያውቀዋል በማለትና ነጻ እንደሚያስወጣው ያግባባው እና የተስፋ ቃል የሰጠው መሆኑን ፖሊስ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ገልጿል።
ከዚህ በኋላ የግል ተበዳዩ ጉዳዩን በማረሚያ ቤት ሆኖ እንዲከታተል ታዞ ማረሚያ ቤት ከወረደ በኋላ ተጠርጣሪው ” አብረውኝ የተማሩ ዳኞቹን እያነጋገርኩልህ ነው፤ ከዳኞቹ ጋር ምሳ አብረን እየበላን ነው ፤ ነጻ እንደምትወጣም ነግረውኛል በማለት ”በስልክ ሲያናግረው እንደነበረ መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል።
በተጨማሪም የግል ተበዳዩ በችሎት በቀጠሮ በሚቀርብበት ዕለት ተጠርጣሪው ችሎት ተገኝቶ ከግል ተበዳይ ኋላ በመቀመጥ ዳኞቹ እንዳዩት ለግል ተበዳይ በመናገር እንዲያምነው በማድረግ እና ዳኞቹ ጋር እየሄድኩ ጉዳይህን እንዳስፈጽም ለመንቀሳቀስ እንዲመቸኝ በማለት የግል ተበዳይ ንብረት የሆነውን ኮድ 2- 10944 የሆነ የቤት መኪና በመውሰድ 1 ዓመት ከ8 ወራት ተሽከርካሪውን ሲጠቀምበት እንደነበር ጠቅሶ ፖሊስ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አብራርቷል።
ከዚህም በኃላ የግል ተበዳዩ ላይ ምስክር ተሰምቶ ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ ለዳኞቹ የሚሰጥ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር እንዲሰጠው በመጠየቅና አስቀድሞ ለቀብድ በሚል 400 ሺህ ብር በተጠርጣሪ ወንድም የንግድ ባንክ ሂሳብ መቀበሉን የገለጸው መርማሪ ፖሊስ ፥ የግል ተበዳይ የጥፋተኝነት ፍርድ ከተሰጠበት በኋላ ደግሞ በገደብ እንድትወጣ አስደርግኃለው በማለት ተጨማሪ 400 ሺህ ብር እንዲሰጠው ጠይቆ በድርድር ላይ እያለ በደረሰ ጥቆማ ባሳለፍነው አርብ ጥር 3 ቀን 2016 ዓ.ም በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ ጠቅሶ የጥርጣሬ መነሻውን ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ገልጿል።
መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪ ዳኛውን በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ የግል ተበዳይና የተጠርጣሪውን ቃል መቀበሉንና የተወሰኑ ማስረጃዎችን መሰብሰቡን ተናግሯል።
ቀሪ የሰውና የሰነድ ማስረጃ ለማሰባሰብ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ገልጾ በወ/መ/ስ/ህ/ቁ 59/1 መሰረት የ14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል።
ተጠርጣሪው በበኩሉ ፥ በቁጥጥር ስር ሲውል በስራ ቦታ ላይ ሆኖ ካለፍርድ ቤት መያዣ መያዙን ጠቅሶ አቤቱታ አቅርቧል።
በተጨማሪም የተጠረጠረበት የወንጀል ድርጊትን አለመፈጸሙን በመግለጽ የግል ተበዳይ ጋር ዝምድና እንዳለውና የእህትማማች ልጆች ነን በማለት አብራርቷል።
በተጨማሪም በወንድሜ ሂሳብ የተቀበልኩት 400 ሺህ ብር ለግል ተበዳዩ ለጠበቃ ማቆሚያ የሚከፈል ነው በማለት ተከራክሯል።
የግል ተበዳይ ተሽከርካሪን በሚመለከት ደግሞ ገራጅ ገብቶ እንደነበር ጠቅሶ ፥ ለተሽከርካሪ የተለያዩ ወጪዎች የሚሆን 55 ሺህ ብር ከፍሎ ከገራጅ አውጥቶ ካቆመበት መኖሪያ ቤት ኢብሳ የሚባል ወንድሙ ወደ ወለጋ ተሽከርካሪውን ይዞ እንደሄደ ተጠርጣሪው ጠቅሶ ተከራክሯል።
ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የዋስትና መብቱን እንዲያከብርለትም ጠይቋል።
መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ÷ ተጠርጣሪው በችሎት የገለጻቸው ሁሉ ሀሰት እንደሆኑና ከግል ተበዳይም ጋር ምንም ዝምድና እንደሌላቸው ገልጿል።
ተጠርጣሪው በሌላ ግለሰብ አማካኝነት በእስር ቤት ሄዶ የግል ተበዳይን ከተዋወቀው በኋላ ጉዳይህን አስፈጽማለሁ ፤ ነጻ አወጣሃለው ፤ ጉዳይህን ከያዙት ከዳኞች ጋር ምሳ እየበላሁ ነው ፤ ነጻ እንደሚያወጡህ ነግረውኛል በማለት ከግል ተበዳይ ጋር የተለዋወጠው የስልክ ልውውጥ ማስረጃ መኖሩን ጠቅሶ ፖሊስ መልስ ሰጥቷል።
በተጨማሪም ፖሊስ ተጠርጣሪው ምስክሮች ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰ መሆኑን ጠቅሶ አመልክቷል።
የግራ ቀኙን ክርክር የተከታተለው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ምርመራው ጅምር ከመሆኑ አንጻር ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መስጠት እንደሚያስፈልግ በማመን የተጠርጣሪውን ዋስትና ጥያቄ ለጊዜው አለመቀበሉን ጠቅሶ የ14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ቀጠሮ ለፖሊስ ፈቅዷል።
በታሪክ አዱኛ