Fana: At a Speed of Life!

ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት የሚደረጉ ኃላፊነት የጎደላቸውን እንቅስቃሴዎች እንደማይታገስ ፖሊስ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ወቅት እና አጋጣሚዎችን እየጠበቁ ሃሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ህዝቡን ለማሸበር እና የፖሊስ ሰራዊቱን ለመከፋፈል የሚደረጉ ሃላፊነት የጎደላቸውን እንቅስቃሴዎች እንደማይታገስ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ፖሊስ አዲስ አበባን የሁከትና የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ ግጭት ጠማቂ ሃይሎች በተለያዩ ጊዜያት ያደረጓቸው ሙከራዎች በፀጥታ ሃይሉ እና በሰላም ወዳዱ የከተማዋ ነዋሪ መክሸፋቸው አስታውሷል፡፡

በዚህ በኩል አልሳካ ያላቸው እነዚህ ፀረ ሰላም ሃይሎች እና የእነሱን አጀንዳ የሚያራግቡ አካላት ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የፖሊስን መልካም ገፅታ ጥላሸት ለመቀባትና ሰራዊቱን ለመከፋፈል ሃሰተኛ መረጃዎችን በመለጠፍ የበሬ ወለደ ወሬ ሲያሰራጩ መቆየታቸውንም አስታውሷል፡፡

አሁን ደግሞ ወቅትና አጋጣሚዎችን ተጠቅመው የሚፈልጉትን አጀንዳ ለማሳካት በለመዱበት መንገድ ሃሰተኛ መረጃ ማሰራጨት ጀምረዋልም ብሏል ፖሊስ፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ በአንድ ብሔር ተወላጆች የፖሊስ አመራርና አባላት ላይ ብቻ ያተኮረ እርምጃዎችን ሊወስድ እንዳሰበ የሚገልፅ ይዘት ያለው ሃሰተኛ ደብዳቤ ልዩ ልዩ ህገ-ወጥ ቴክኒኮችን በመጠቀም በማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ ሲያዘዋወሩ ተስተውሏልም ነው ያለው፡፡

አክሎም ፖሊስ ፥ እውነታውን መላው የተቋማችን አመራርና አባላትም ሆኑ የከተማችን ነዋሪዎች የሚያውቁት በመሆኑ ለተሰራጨው ሃሰተኛ መረጃ ቦታ ባለመስጠት ሁከትና ግጭት ለመፍጠር እንዲህ አይነቱን ህገ ወጥ ተግባር የሚፈፅሙ ግለሰቦችን እና ቡድኖችን በማጋለጥ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ተቀናጅተው መስራታቸውን ይቀጥላሉ ብሏል፡፡

ሰላም ወዳዱ የከተማዋ ነዋሪ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሰላምን ደህንነትን ለማስጠበቅ የሚከናወኑ ተግባራትን በማገዝ ተባባሪነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ነው ፖሊስ ጥሪውን ያስተላለፈው፡፡

በዚህም የአዲስ አበባ ፖሊስ በአንድ ብሔር ተወላጅ በሆኑ የፖሊስ አመራርና አባላት ላይ ብቻ ያተኮረ እርምጃዎችን ሊወስድ እንዳሰበ ተደርጎ በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ ሲያዘዋወር የተስተዋለው መረጃ ሐሰተኛ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.