ክልሎቹ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰድን ነው አሉ
አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ መሆኑን የኦሮሚያ እና አማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮዎች ገለጹ፡፡
የኦሮሚያ ክልል ንግድ ቢሮ የዋጋ ግሽበቱን ለማረጋጋት አምራቹ እና ሸማቹ በቀጥታ የሚገናኙበትን አዳዲስ የገበያ ማዕከላትን እያስፋፋሁ ነው ብሏል፡፡
በክልሉ በተለያዩ ከተሞች 270 የሰንበት ገበያ እየተተገበረ መሆኑን ነው የቢሮው ምክትል ሃላፊ ክፍሌ ታደሰ የተናገሩት፡፡
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት 1ነጥብ 5 ቢሊየን ተዘዋዋሪ ገንዘብ መመደቡን ገልጿል፡፡
በተጨማሪም ዘመናዊ የገበያ የንግድ ስርዓትን መገንባት ላይ ትኩረት መሰጠቱንም ነው የቢሮው ምክትል ኃላፊ ብዙዓለም ግዛቸው የገለጹት፡፡
ክልሎቹ ምርት በስፋት ከተመረተባቸው አካባቢዎች ወደ ሌሎች አካባቢዎች የገበያ ትስስር መፍጠራቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል፡፡
በአማራ ክልል የሰላም መደፍረስን ተከትሎ የነዳጅ የገበያ ስርዓቱን ወደ ጎን ብለው በህገወጥ መንገድ ለመሸጥ በሞከሩ የነዳጅ ማደያዎች ላይ እርምጃ መወሰዱም ነው የተነገረው፡፡
ክልሎቹ ሕገወጥ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊ እና ሕጋዊ እርምጃ መውሰዳቸውም ተጠቅሷል፡፡
በአልማዝ መኮንን