በአማራ ክልል በድርቅ ጉዳት ለደረሠባቸው አካባቢዎች የሚደረገው ድጋፍ መቀጠሉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በድርቅ ጉዳት ለደረሠባቸው አካባቢዎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን የአማራ ክልል መንግሥት አስታወቀ፡፡
የክልሉ መንግሥት መረጃ እንደሚያሳየው አሁን ላይ በሰሜን ጎንደር፣ ዋግኸምራ እንዲሁም ሰሜን ወሎ አካባቢዎች ድርቅ ተከሥቷል።
የተከሠተው ድርቅ የከፋ ጉዳት ከማድረሡ በፊት ከፌደራል መንግሥትና አጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ስለመሆኑም ነው የክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋሥትና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተሥፋው ባያብል ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት።
እስካሁንም በመጀመሪያው ዙር ከ1ሚሊየን በላይ ወገኖች ድጋፍ እንዲደርሳቸው ተደርጓል ነው የተባለው።
በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት ከፌደራል መንግሥት ጋር በቅንጅት በመሆን ሁለተኛ ዙር እርዳታ ወደ አካባቢዎቹ እየደረሰ ነውም ተብሏል።
በክልሉ የተከሠተውን ድርቅ ለመቋቋም እንዲቻልም ሁሉም አካል ርብርብ ሊያደርግ ይገባልም ነው ያሉት ኮሚሽነሩ።
በሰለሞን ይታየው