አቶ ደመቀ መኮንን ከዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ፕሬዚዳንት ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ፕሬዚዳንት ቦርግ ብሬንድ ጋር ውይይት ተወያዩ፡፡
ውይይቱ የተካሄደው ለ54ኛ ጊዜ በዳቮስ ስዊዘርላንድ እየተካሄደ ከሚገኘው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ጎን ለጎን ነው፡፡
በውይይታቸውም በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ የምጣኔ ሃብት እምርታዎች አቶ ደመቀ ማብራራታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
እድገትን ለማስቀጠል እና የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ መንግስት መሰረታዊ ማሻሻያዎችን ማድረጉንም አስረድተዋል፡፡
ቁልፍ የሆኑ የመሰረተ ልማት አውታሮችን ለማስፋፋት መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው÷ ኢትዮጵያ በራስ አቅም የገነባችውን ታላቁ የኢትትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡
የአገልግሎት ዘርፉን ተደራሽ ለማድረግ፣ የፋይናንስ ተቋማትን ለማሻሻልና የግሉን ክፍለ-ኢኮኖሚ ድርሻ ለማሳደግ መንግስት የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
ቦርግ ብሬንድ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ በየዓመቱ በሚካሄደው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ጉባዔ ላይ ለዓመታት ሳታቋርጥ ለቀጠለችው ተሳትፎ ምስጋና አቅርበዋል።
ፎረሙ በቀጣይ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ መቀጠል እንደሚፈልግም አመላክተዋል፡፡