Fana: At a Speed of Life!

በጄኔራል አበባው ታደሠ የተመራ ልዑክ በአዋሽ አርባ የሜካናይዝድ ኃይልን ጎበኘ

አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሠ የተመራ የከፍተኛ አመራሮች ልዑክ በአዋሽ አርባ የሚገኘውን የሜካናይዝድ ኃይልን ጎብኝቷል፡፡

ልዑኩ የሜካናይዝድ ሃይሉን የሥልጠና ሂደት የተመለከተ ሲሆን÷ ከምልከታው በኋልም ጄኔራል አበባው ታደሠ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም÷ ለኢትዮጵያ ዕድገት እንቅፋት ለመፍጠር የሚጥሩ ጠላቶችና እና አዳዲስ ኃይሎች እየተሰባሰቡ እንዳለ እያየን ነው ብለዋል፡፡

ጠላቶች ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ በቅርበት እየተከታተልን እንገኛለን ያሉት ጄኔራል አበባው÷ ኢትዮጵያ የማንንም ሀገር ብሔራዊ ጥቅም መንካት ተገቢ አለመሆኑን በማመን የሌላ ሀገር ብሔራዊ ጥቅም ነክታ አታውቅም አሁንም አትነካም ታሪኳም አይደለም ብለዋል።

የሌላን ሀገር ብሔራዊ ጥቅም እንደማንነካው ሁሉ እኛም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፈን አንሰጥም በማለት ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብሔራዊ ጥቅም እንደወትሮው ሁሉ ዛሬም ዘብ እንቆማለን ሲሉ ገልፀዋል፡፡

የሜካናይዝድ ኃይልም ዘመናዊነትን በመከተል ኢትዮጵያን በሚመጥናት ልክ የጀመረውን ሥልጠና በማዳበር እና ወቅታዊ ትኩረት በመሥጠት በአዳዲስ እና ዘመናዊ ትጥቆች ሙያዊ ብቃታትን ማዳበርና ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

በስነ-ልቦና ዝግጁነት ብቁ በመሆን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም እና ክብር መረጋገጥ ሲባል የምትወስዱትን ሙያዊ ስልጠና በፍጥነት ማጠናቀቅና ለሚሰጣችሁ ማንኛውም ግዳጅ ዝግጁ መሆን ይጠበቅባችኋል ሲሉ አፅንኦት መስጠታቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመላክታል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.