የኮፕ 28 ጉባዔ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር የካርቦን ልቀትን ለመከላከል ውጤታማ መሆኑ የታየበት ነበር ተባለ
አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮፕ 28 ጉባዔ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር የካርቦን ልቀትን በመከላከል ረገድ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ማሳየት የተቻለበት እንደነበር የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሐብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮን መሪ ከሆኑት ፈርዲናንድ ቮን ዌይ ጋር ውይይት በተካሄደበት ወቅት ነው፡፡
በነበራቸው ቆይታም÷ በኢነርጂ ልማት፣ በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አቅርቦት እንዲሁም በውሃ ሐብት አሥተዳደር ሥራዎች ላይ ፍሬያማ ውይይት ማካሄዳቸው ተገልጿል፡፡
የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ሡልጣን ወሊ(ዶ/ር ኢ/ር ) በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ልማት ዘርፍ አበረታች ሥራዎች እያከናወነች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቅይጥ የኢነርጂ አማራጮች ላይም ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ እንደሆነና “ግሪን ሃይድሮጅን”ንም በኢትዮጵያ ለማምረት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ነው ጨምረው ማብራራታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።
የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አሥፋው ዲንጋሞ÷ የጀርመን ድርጅቶች በኢትዮጵያ ለከተሞች ግዙፍ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ፕሮጀክቶች ማሥፈጸሚያ የሚሆን ብድር የሚያቀርቡበትን ሁኔታ እንዲመለከቱ ጠይቀዋል፡፡
ከጂአይዜድ ኢትዮጵያ ጋር በሐዋሳ እና በዝዋይ ሐይቆች አካባቢ የውሃ ሐብት አሥተዳደር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውም የተጠቆመ ሲሆን÷ የጀርመን ምሁራን በተቀናጀ የውሃ ሐብት አሥተዳደር ላይ ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ የውሃ ሐብት አሥተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ አብርሃ አዱኛ (ዶ/ር) ጠይቀዋል፡፡