በመዲናዋ ሰላምን ለማረጋገጥ የሴቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የሴቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ገለፀ፡፡
ቢሮው በመጭው አርብ እና ቅዳሜ የሚከበሩትን የከተራና ጥምቀት በዓላት አስመልክቶ ከሁሉም ክፍለከተሞች ከተወጣጡ የሴት አደረጃጀት አባላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
የአስተዳደሩ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ ሊዲያ ግርማ በመድረኩ እንደተናገሩት÷ ፀረ ሰላም ሀይሎች በመዲናዋ ሽብር ለመፍጠር የሚያደርጉትን ሙከራ በማክሸፍ ረገድ ሴቶች ከፍተኛ ሚና ነበራቸው፡፡
የከተራ እና ጥምቀት በዓላት ሀይማኖታዊ ትውፊታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ ሴቶች እና መላው የከተማዋ ነዋሪዎች ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶችና ሕጻናት ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ ወይንሸት ዘሪሁን በበኩላቸው÷ የጥምቀት በዓል በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎች የሚሳተፉበት የአደባባይ በዓል መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በመሆኑም በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ወጣት፣ ሴቶችና እናቶች የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡