Fana: At a Speed of Life!

ከሶማሊላንድ ጋር የተፈረመው የትብብርና አጋርነት ሰነድ በጋራ መልማትን የሚያረጋግጥ ነው – ዲማ ነገዎ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቅርቡ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈረመው ሁሉን አቀፍ የትብብርና አጋርነት ሰነድ በጋራ መልማትን የሚያረጋግጥ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ዲማ (ዶ/ር)÷ በፈረንሳይ ፓርላማ የሀገር መከላከያና የጦር ሃይሎች ኮሚቴ ሰብሳቢ ቶማስ ጋሲሉድ የተመራውን ልዑክ ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

በዚህ ወቅትም ኢትዮጵያ በቅርቡ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው ሁሉን አቀፍ የትብብርና አጋርነት ሰነድ በጋራ መልማትን የሚያረጋግጥ ሰነድ መሆኑን ለቡድኑ አብራርተዋል፡፡

ኤርትራ ነጻነቷን ካገኘች በኋላ ኢትዮጵያ የባሕር በር ተዘግቶባት የቆየች ሀገር እንደሆነች ማስታወሳቸውን የምክር ቤሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

ለረጅሙ ሀገራዊ እና የምጣኔ ሃብታዊ ደህንነት በሰጥቶ መቀበል መርህ ከሶማሊ ላንድ ጋር የተደረሰው ሁሉን አቀፍ የትብብርና አጋርነት ስምምነት ሰነድ በጋራ ለመልማት ሚናው ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሰነዱን በተመለከተ በቅርቡ የአውሮፓ ሕብረት የተዛባ አስተያየት ማንፀባረቁን እና በሕብረቱ የተሰጠው አስተያየት ትክክል እንዳልሆነ የፈረንሳይ መንግስት እንዲገነዘበው ለልዑኩ ጠቁመዋል።

የባሕር በሩ አካባቢ ጸጥታ የኢትዮጵያን አስተዋጽዖ እንደሚጠይቅ የገለጹት ሰብሳቢው÷ የተፈረመው የትብብርና አጋርነት ሰነድ ወደ ተግባራዊ ምዕራፍ እንዲሸጋገር ፈረንሳይ የበኩሏን እገዛ እንድታደርግ ጠይቀዋል፡፡

በፈረንሳይ ፓርላማ የሀገር መከላከያና የጦር ሃይሎች ኮሚቴ ሰብሳቢ ቶማስ ጋሲሉድ በበኩላቸው÷ ፈረንሳይ በማሕበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ዘርፎች ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.