አቶ ደመቀ መኮንን ከፓኪስታን ባለአደራ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከፓኪስታን ባለአደራ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዋር ኡል ሃቅ ካካር ጋር ተወያዩ፡፡
ውይይቱ በስዊዘርላንድ ዳቮስ ክሎስተር እየተካሄደ ከሚገኘው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ጎን ለጎን የተካሄደ ነው፡፡
የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ትብብርን የበለጠ ለማጠናከር በተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት እርከኖች በሚገኙ የጋራ ጉዳዮች ላይ ነው የመከሩት።
አቶ ደመቀ መኮንን፥ ኢትዮጵያ ኤምባሲዋን በኢስላማባድ በቅርቡ መክፈቷን በመጥቀስ የኢትዮ-ፓኪስታንን ግንኙነት ለማጠናከር ኢትዮጵያ ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ከፓኪስታን ጋር ንግድና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ የተለያዩ ግንኙነቶችን ለማጠናከር እንደምትሰራ መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ባለአደራ ጠቅላይ ሚኒስትር ካካር በበኩላቸው እንዳሉት፥ የፓኪስታን እና የኢትዮጵያ መንግስታት ለሁለትዮሽ ግንኙነታቸው ማደግ ያላቸውን ቁርጠኝነት በመጠቀም ሀገራቸው በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ክህሎት ሽግግር እንዲሁም በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ላይ ትስስሯን ለማጠናከር ትሰራለች።
በአሁኑ ጊዜ የፓኪስታን ባለአደራ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በማገልገል ላይ ያሉት አንዋር ኡል ሃክ ካካር የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍን በፈረንጆቹ ነሐሴ 2023 በመተካት ነው፡፡
በፓኪስታን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኤምባሲ በፈረንጆቹ ግንቦት 11 ቀን 2023 በይፋ ተመርቆ የተጀመረ ሲሆን፥ አምባሳደር ጀማል በከር የመጀመሪያው ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡