የ78 ዓመት ወላጅ እናቱን የገደለው ተከሳሽ በፅኑ እስራት ተቀጣ
አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ78 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ወላጅ እናቱን የገደለው ተከሳሽ በጽኑ እሥራት መቀጣቱን ፍትሕ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
አዲስ አስራት ይመር የተባለው ተከሳሽ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 ደብረሰላም ትምህርት ቤት አካባቢ ከ78 ዓመት ወላጅ እናቱ ጋር ይኖር እንደነበር ሚኒስቴሩ በመረጃው አመላክቷል፡፡
ተከሳሹ ጥር 16 ቀን 2015 ዓ.ም ከሌሊቱ በግምት 11 ሠዓት ሲሆንም የ78 ዓመት ወላጅ እናቱ ካስቀመጣቸው ሶፋ መሬት ላይ ወድቀው ሲያገኛቸው በእጁ አንገታቸውን አንቆ በመያዝ ሕይወታቸው እንዲያልፍ ማድረጉን ጠቅሷል፡፡
ጉዳዩን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በምርመራ አጣርቶ፣ በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን የሚከታተለው ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት በወ/ሕ/አ 540 መሠረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ክስ ቀርቦበት ክርክር ሲደረግ መቆየቱንም ከፍትሕ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ነበር ተብሏል፡፡
ተከሳሹም÷ የመከላከያ ምስክሮች ማስረጃነት አቅርቦ ያሰማ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ የቀረበለትን ክስ መከላከል ባለመቻሉ ፍርድ ቤቱ የጥፋተኛነት ፍርድ ሰጥቷል፡፡
በዚህም ተከሳሽ በ10 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑ ተገልጿል፡፡