በመዲናዋ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ከ746 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ተገኘ
አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሥድስት ወራት ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ከ746 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱ ተገለጸ፡፡
ገቢው የተገኘው 44 ሺህ ቶን ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል መሆኑን የአዲስ አበባ ፅዳት አሥተዳደር ኤጀንሲ ገልጿል።
በኤጀንሲው የመልሶ መጠቀምና ዑደት ማዕከል ዳይሬክተር ባዩሽ ታደሰ እንደገለጹት÷ ኤጀንሲው የመዲናዋን ፅዳትና ውበት ከማስጠበቅ ባለፈ ቆሻሻን መልሶ በመጠቀም የገቢ ምንጭ እያደረገ ነው፡፡
በዚህም በሥድስት ወራት 636 ሚሊየን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ፤ ከዕቅድ በላይ ከ746 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሠብሰቡን ነው የተናገሩት፡፡
ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም የ14 በመቶ ብልጫ የተገኘበት እንደሆነ ነው የተጠቆመው።
በመዲናዋ ቆሻሻን መልሶ በመጠቀም ዘርፍ ከ300 በላይ ማኅበራት ተደራጅተው እየሰሩ መሆናቸውንም አስታውሰዋል፡፡
በዚህም በግማሽ ዓመቱ ብቻ ለ480 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለ ነው ያስረዱት፡፡
ባለፈው በጀት ዓመት ከ86 ሺህ ቶን በላይ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢዜአ ዘገባ አመልክቷል።