የከተራና ጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር ወደ ሥራ መግባቱን ግብረ-ኃይሉ አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2016 ዓ.ም የከተራና ጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር ዕቅድ አውጥቶ ወደ ሥራ መግባቱን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታውቋል፡፡
የከተራና ጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር የፀጥታ አካላት ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ ሥራ መግባታቸውንም ነው ግብረ-ኃይሉ ያስታወቀው፡፡
በዓሉ በሰላም እንዲከበር ሊከናወኑ በሚገባቸው ተግባራት ዙሪያም ምክክር መደረጉ ተገልጿል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ ኃላፊ ም/ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ በውይይቱ ላይ እንዳሉት÷ ፀረ-ሰላም ኃይሎች የበዓሉን አከባበር ድባብ ለማደፍረስ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ግጭት ቀስቃሽ ይዘት ያላቸው መረጃዎችን እያሰራጩ ነው፡፡
ሰላም ጠል የሆኑ ቡድኖች አለን ለማለት ያላቸውን አቅም በመጠቀም ጉዳት ለማድረስ ወደ ኋላ እንደማይሉም አመላክተዋል፡፡
ይሁን እንጂ በዓሉ በሰላም እንዲከበር ሁሉም አመራርና አባል ኃላፊነቱን በብቃት ሊወጣ ይገባል ማለታቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው÷ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ከማህበረሰቡ እና ከሐይማኖት አባቶች ጋር ውይይት መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በ2016 ዓ.ም ሕዝብ በስፋት ወደ አደባባይ በመውጣት ያከበራቸው ሐይማኖታዊ በዓላት እና ሌሎች ልዩ ልዩ ኩነቶች በሰላም መከበራቸውን አስታውሰዋል፡፡
ከተራና ጥምቀትን ሕብረተሰቡ ያለስጋት እንዲያከብርም የፀጥታ አካላት በቴክኖሎጂ ታግዘው ወደ ተግባር መግባታቸውንም አስታውቀዋል፡፡
በበዓሉ አከባበር ብሄርን ከብሄር፣ ሐይማኖትን ከሐይማኖት፣ የሚያጋጩ ጭፈራዎች፣ አልባሳቶች፣ ጽሑፎች እና ግጭት ቀስቃሽ ተግባራትን የማይታገስ መሆኑንም የጋራ ግብረ-ሃይሉ በአጽንኦት ገልጿል።