በሀሰተኛ ሰነዶች ግለሰቦች ሳያውቁ ቤታቸውን ለመሸጥ ከ15 ሚሊየን ብር በላይ የተቀበለው ተከሳሽ በእስራትና በገንዘብ ተቀጣ
አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም ግለሰቦች ሳያውቁ ቤታቸውን ለመሸጥ ከ15 ሚሊየን ብር በላይ ተቀብሏል የተባለው ተከሳሽ በጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጣ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ወሰነ።
በአ/አ ከተማ ኮልፌ ቀራንዮ ኗሪና በግል ስራ የሚተዳደረው ተካ ዲኖ ሰይድ የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 ንዑስ ቁጥር 2(ሀ) እና ንዑስ ቁጥር 3 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ በተዘጋጁ ሀሰተኛ መንግስታዊ ሰነዶች መገልገል የሙስና ወንጀል እና በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል በፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ ክስ ቀርቦበት ነበር።
ከቀረቡበት ክሶች መካከል ተከሳሹ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለራሱ ለማግኘት፤ ለሌሎችም ለማስገኘት በማሰብ በመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም ከስንታየው አበበ አወቀ ያልተሰጠውን ሀሰተኛ የውክልና ሰነድ፤ ሃሰተኛ የመሬት ይዞታ መብት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት እና ሃሰተኛ ያላገባ የምስክር ወረቀት በመጠቀም በፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ጽ/ቤት አቅርቦ ሽያጭ ውል መፈጸሙ ተመላክቷል።
በፈጸመው የሽያጭ ውል መሰረት ደግሞ በስንታየው አበበ ስም ተመዝግቦ በኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ ወረዳ 07 የሚገኘውን የቦታው ስፋት 94 ነጥብ 64 ካ/ሜትር የሆነ ጅምር የመኖሪያ ቤት ለግል ተበዳይ እንዳለ መኩሪያ ለመሸጥ በመስማማት በቅድሚያ 5 ሚሊየን 100 ሺህ ብር በባንክ ሂሳቡ እንዲገባለት በማድረግ እና የገባለትንም ገንዘብ ወደ ተለያዩ ግለሰቦች ሂሳብ በማስተላለፍ በሃሰት በተዘጋጁ መንግስታዊ ሰነዶች መገልገል የሙስና ወንጀል ተከሷል፡፡
በሁለተኛው ክስ ደግሞ ተከሳሹ ንብረትነቱ የአሊ ሃይረዲን መሃመድ የሆነ በኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ ወረዳ 07 የቤት ቁጥር አዲስ የሚገኘውን የመኖሪያ ቤት ለመሸጥ እንዲያስችለው በሃሰተኛ የተለያዩ ሰነዶችን በመጠቀም ከባለንብረቱ ያልተሰጠውን ውክልና እንደተሰጠው በማስመሰል ከመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ ቅ/ጽ/ቤት ያልተሰጠ ተመሳስሎ የተዘጋጀ የመሬት ይዞታ መብት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ኮፒ እና ከኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ ወረዳ 05 ወሳኝ ኩነት የተሰጠ የሚል ሃሰተኛ የባለንብረቱ ያላገባ የምስክር ወረቀት ቅጂ በማቅረብ ቤቱን በ40 ሚሊየን ብር ለግል ተበዳይ እድሪስ ቡንሱር አብደላ ለመሸጥ መስማማቱ በክሱ ተጠቅሷል።
በግንቦት 9 ቀን 2014 ዓ.ም ደግሞ የመንደር ሽያጭ ውል የተፈረመ ቅድሚያ ክፍያ 10 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ከግል ተበዳይ እድሪስ ቡንሱር የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ቤተል ቅርንጫፍ ወደ ተከሳሽ የባንክ ሂሳብ ዝውውር የተፈጸመለት መሆኑም በክሱ ተጠቅሷል።
በአጠቃላይ ተከሳሽ ከአሊ ሃይረዲን ያልተሰጠውን ውክልና ሰነድ፣ ሃሰተኛ የመሬት ይዞታ መብት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት እና ሃሰተኛ ያላገባ የምስክር ወረቀት በማቅረብና የሽያጭ ውል በመፈጸም 10 ሚሊየን 500 ሺህ ብር በባንክ ሂሳቡ እንዲገባለት በማድረግና ገንዘቡን ወደተለያዩ ግለሰቦች ሂሳብ በማስተላለፍ ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለራሱ እና ለሌሎችም ያስገኘ በመሆኑ በፈጸመው በሃሰት በተዘጋጁ መንግስታዊ ሰነዶች መገልገል የሙስና ወንጀል ተከሷል፡፡
ከ4ኛ እስከ 5ኛ ባሉ ክሶች ላይ ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ ግለሰቦች በባንክ ሂሳቡ የገባለትን ከ15 ሚሊየን ብር በላይ ለመደበቅ እና ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ በማሰብ ገንዘቡን በተለያዩ ግለሰቦች ስም በተለያዩ መጠኖች በማስተላለፍ እንዲሁም በራሱ ስም ደግሞ በባንክ በተከፈተ ሂሳቡ ከ1 ሚሊየን ብር በላይ ያስተላለፈ መሆኑ ተጠቅሶ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ በማቅረብ ወንጀል ተከሶ ነበር።
ተከሳሹ በዚህ መልኩ የቀረቡበት የወንጀል ድርጊት አለመፈጸሙን ጠቅሶ የሰጠውን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ የሰውና የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል።
የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን የመረመረው ችሎቱ ተከሳሹ እንዲከላከል ብይን የሰጠ ቢሆንም ማስረጃዎቹን ማስተባበል ባለመቻሉ ተከላከል በተባለበት ድንጋጌ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎበታል።
ዐቃቤ ሕግ የቅጣት ማክበጃ አስተያየት፤ በተከሳሹ በኩል ደግሞ ሰባት የቅጣት ማቅለያ አስተያየት በጽሁፍ ቀርበዋል።
የግራ ቀኙን አስተያየት የመረመረው ፍርድ ቤቱ ሰባት የቅጣት ማቅለያ በመያዝ በዕርከን 23 መሰረት ተከሳሹ በ11 አመት ጽኑ እስራትና በ10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።
በታሪክ አዱኛ