Fana: At a Speed of Life!

ጥምቀትን በደምበል ሐይቅ ደሴቶች ለማክበር ከ20 ሺህ በላይ እንግዶች ይጠበቃሉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተራ እና ጥምቀት በዓል በልዩ ሁኔታ በሚከበርበት የደምበል ሐይቅ ደሴቶች ከ20 ሺህ በላይ እንግዶች እንደሚጠበቁ የባቱ ከተማ ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ገለጸ፡፡

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ከድር አቢቲ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት÷ በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ፣ እንግዶችም በቂ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል ኮሚቴ ተዋቅሮ በቅንጅት ሲሠራ ቆይቷል፡፡

በዓሉ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበርም ሁሉም የድርሻውን ሥራ እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው÷ ፖሊስን ጨምሮ ሌሎች የጸጥታ አካላትም ሥራቸውን በትጋት እያከናወኑ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

የከተማው ነዋሪም ከጸጥታ አካላት ጎን ሆኖ ሥራዎችን እንዲያግዝ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያለሙ ውይይቶች መካሄዳቸውን ተናግረዋል፡፡

በዓሉ በሚከበርበት አካባቢም በበዓሉ ቀን መድረኩ በሌሎች አካላት እንዳይያዝ አቅጣጫ ተላልፏል ነው ያሉት።

በበዓሉ ወቅት ወደ ከተማዋ ይመጣሉ ተብሎ የሚጠበቁ እንግዶችን ለማስተናገድ የሚያስችሉ የመኝታ፣ የምግብና መጠጥ አገልግሎቶች በንግዱ ማኅበረሰብ ዘንድ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.