አገልግሎቱ 496 ሺህ በላይ ጉዳዮችን በማስተናገድ 1 ነጥብ 29 ቢሊየን ብር ገቢ አገኘ
አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 496 ሺህ 359 ጉዳዮችን በማስተናገድ ከ1 ነጥብ 29 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት አስታውቋል፡፡
የአገልግሎቱ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ አለምሸት መሸሻ እንደገለጹት÷ በ2016 በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት የተቀመጠውን እቅድ ከማሳካት አንጻር ስኬታማ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡
በዚህ መሰረትም በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ለ877 ሺህ 722 ተገልጋዮች አገልግሎት መስጠት መቻሉን አንስተዋል፡፡
ከተለያዩ አገልግሎት ዘርፎች 932 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ለማግኘት ታቅዶ 1 ነጥብ 292 ቢሊየን ብር ማግኘት መቻሉን ነው የተናገሩት፡፡
በሌላ በኩል 374 ሺህ 951 የሚሆኑ አገልግሎቶች በኦንላይን የአሰራር ስርዓት ታግዘው ለደንበኞች መሰጠታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራትም ተቋሙ በቀን በአማካይ 6 ሺህ 649 ተገልጋዮችን ካለቀጠሮ ማስተናገድ መቻሉን አቶ አለምሸት ጠቁመዋል፡፡
908 ሃሰተኛ ሰነዶች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ መደረጋቸውን ጠቅሰው÷ ከዚህ ውስጥም 749 የሚሆኑት ሃሰተኛ የማንነት መታወቂያዎች ናቸው ብለዋል፡፡
ወንጀልንን በጋራ ለመከላከል ከክልሎች፣ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ እና ከተለያዩ የፍትሕ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ